የሀገር ውስጥ ዜና

ከግንባታ ስራዎች ወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ እየተደረገ ነው

By Amele Demsew

March 15, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከግንባታ ሥራዎች ጋር ተያይዞ የወሰን ማስከበርና የካሳ ክፍያ ጉዳዮችን በአግባቡ ለመስራት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወንድሙ ሴታ(ኢ/ር)÷ የዜጎችን የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።

እነዚህ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች በተያዘላቸው በጀትና የጊዜ ገደብ ተጠናቀው ለዜጎች አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህ ሂደትም የወሰን ማስከበርና የካሳ ክፍያ አከፋፈል ሥርዓት በተለይም የካሳ ክፍያ መጋነን ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት እንዳይጠናቀቁ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህ መነሻነትም የወሰን ማስከበርና የካሳ ክፍያ ችግሮችን በዘላቂትነት ለመፍታት የሕግ ማሻሻያ ለማድረግ ረቂቂ ሕግ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኳል ነው ያሉት፡፡

የሚሻሻለው ሕግ የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን፣ ካሣ የሚከፈልበትና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 1161/2011 መሆኑን ጠቁመዋል።

የተሻሻለው ሕግ ጸድቆ ወደ ሥራ ሲገባ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማቃለል ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብና በጀት እንዲጠናቀቁ በማድረግ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡