የሀገር ውስጥ ዜና

የዜጎች የፍትህ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

By Amele Demsew

March 15, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዜጎች የፍትህ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሚመራበት የአሰራር ሥነ ስርዓት ደንብ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት እየተካሄ ነው።

በውይይቱ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘው ተሻገር እንዳሉት÷ ላለፉት ጊዜያት የህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ከህገ መንግስት ጋር የተቃረኑ አሰራሮችን በማጣራት ለምክር ቤቱ ሲያቀርብ ቆይቷል።

ጉባኤው በሀገሪቱ ትልቁ የህግ ተቋም እንደመሆኑ የአሰራር ሥነ-ስርዓቱ መዘጋጀቱ ትርጉም የሚያስፈልጋቸውን የውሳኔ ሀሳቦች ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በማቅረብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የዜጎች የፍትህ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በእጅጉ ያግዛል ብለዋል።

የጉባኤው ሰብሳቢ እና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በበኩላቸው÷ ጉባኤው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ህገ መንግስታዊ ጉዳዮችን እየመረመረ እና ውሳኔ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

የሚቀርቡለትን የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄዎችና አቤቱታዎች የማጣራት ስራውን በፍጥነት እና በግልፅነት ለማቅረብ የሚመራበት የአሰራር ስነ- ስርዓት ደንብ መቀረፁን አንስተዋል፡፡

በዚህም የአሰራር ስነ- ስርዓት ደንቡ ላይ የተለያዩ ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ረቂቅ ሰነዱም ውይይት ከተካሄደበት በኋላ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይቀርባል ነው የተባለው፡፡

በምንይችል አዘዘው