የሀገር ውስጥ ዜና

የመዲናዋ 3 የገበያ ማዕከሎች በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተገለጸ

By Amele Demsew

March 15, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡት ሶስት ትላልቅ የገበያ ማዕከሎች በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡

አገልግሎት መስጠት የጀመሩት የኮልፌ እና ለሚ ኩራ የግብርና ምርቶች መሸጫ እንዲሁም የአቃቂ ቃሊቲ የሰብል ምርቶች መሸጫ ማዕከላት መሆናቸው ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ 57 አምራች እና አቅራቢዎች ካባለፈው ሳምንት ጀምሮ በገበያ ማዕከላቱ ምርት እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡

በጨረታ ተለይተው ወደገበያ ማዕከላቱ እንዲገቡ የተደረጉት የራሳቸው መሬት ኖሯቸው ዓመቱን ሙሉ ማምረት እና ማቅረብ የሚችሉ አምራቾች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም÷ 147 ቸርቻሪ ነጋዴዎች ምርቶቻቸውን እያቀረቡ ሲሆን በመዲናዋ የሚገኙ 11 ማህበራትም ምርት እንዲያቀርቡ ስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል፡፡

በገበያ ማዕከላቱ የሚቀርቡ ምርቶች ከመደበኛው ገበያ ጋር ሲነጻጸሩ ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ እንዳላቸውም አንስተዋል፡፡

የዋጋ ንረትን ለመቋቋም የገበያ ማዕከላቱ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑንም አቶ ሰውነት አየለ ገልጸዋል።

በመሳፍንት እያዩ