አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኩላሊት ሥራውን ቀስ በቀስ እየቀነሰ ሲመጣ ሥር የሰደደ የኩላሊት ህመም ይከሰታል፡፡
ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኩላሊት ጤና ታስቦ የዋለ ሲሆን ÷ይህን ታሳቢ በማድረግ ስለ ሥር የሰደደ የኩላሊት ህመም ቢያውቁ ያልናቸውን እናጋራችሁ፡፡
ኩላሊት ቆሻሻ እና ከመጠን በላይ ፈሳሽን ከደም ያጣራል፤ ከዚያም በሽንት አማኝነት ይወገዳል፡፡
ሆኖም ሥር የሰደደ የኩላሊት ህመም ተጠቂ ሲሆኑ ፥ በሰውነትዎ ውስጥ አደገኛ የሆነ ፈሳሽ፣ ኤሌክትሮላይት እና ቆሻሻ እንዲከማች ያደርጋል።
የኩላሊት ህመም የመጀመሪያ ደረጃዎች ላይ ጥቂት ምልክቶች ሊታይ ይችላል። በአንጻሩ ሁኔታው ሥር የሰደደ እስከሚሆን ድረስ የኩላሊት ህመም እንዳለቦዎ ላያውቁም ይችላሉ።
ሥር የሰደደ የኩላሊት ህመም ሕክምና ብዙውን ጊዜ መንስኤውን በመቆጣጠር የኩላሊት መጎዳትን ፍጥነት መቀነስ ላይ ያተኮረ ቢሆንም የህመሙን መንስኤ መቆጣጠር ኩላሊት እንዳይጎዳ ማድረግ ሊያዳግተው እንደሚችል ከማዮ ክሊኒክ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ሥር የሰደደ የኩላሊት ህመም ወደ መጨረሻው ደረጃ ኩላሊት ስራውን እስከማቆም ሊደርስ የሚችል ሲሆን ፥ ይህ ደግሞ ሰው ሰራሽ ማጣሪያ (ዲያሊሲስ) ወይም የኩላሊት ንቅለ ተከላ ካልተደረገ ለሞት ይዳርጋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሥር የሰደደ የኩላሊት ህመም ምልክቶች ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ድካም፣የእንቅልፍ ማጣት ችግር፣ብዙ ወይም ያነሰ ሽንት መኖር፣የጡንቻ መኮማተር፣የእግር እና የቁርጭምጭሚት እብጠትና ደረቅና የሚያሳክክ ቆዳ መኖር ናቸው፡፡
እንዲሁም ለመቆጣጠር አስቸጋሪ የሆነ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ በሳንባ ላይ ፈሳሽ ከተፈጠረ የአተነፋፈስ መቆራረጥ እና በልብ ዙሪያ ፈሳሽ ከተፈጠረ በደረት ላይ የሚሰማ ህመም ሥር ከሰደደ የኩላሊት ህመም ምልክቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
ሥር ከሰደደ ኩላሊት ህመም አባባሽ ምክንያቶች ውስጥ ደግሞ የስኳር ህመም፣ከፍተኛ የደም ግፊት፣የልብ ህመም፣ማጨስ፣ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣የኩላሊት ህመም ያለበት የቤተሰብ ታሪክ መኖር፣ያልተለመደ የኩላሊት አፈጣጠር፣የዕድሜ መግፋት እና ኩላሊትን ሊጎዱ የሚችሉ መድሃኒቶችን አዘውትሮ መጠቀምና ይጠቀሳሉ፡፡
አለማጨስ፣የሰውነት ክብደትን መመጠን፣ጤናማ የሆነ አመጋገብ መከተልና ያለ ሃኪም ትዕዛዝ መድሃቶችን አለመውሰድ ደግሞ ሥር የሰደደ የኩላሊት ህመም መከላከያ መንገዶች ናቸው፡፡