ስፓርት

41 ሀገራትን አቆራርጦ አዲስ አበባ የገባው የሠላም ተጓዥ ብስክሌተኛ

By Amele Demsew

March 12, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሞሮኮ ራባት የተነሳው ኮትዲቯራዊ የሠላም ተጓዥ ብስክሌተኛ ካቮሬ ካሪን 41 ሀገራትን አቆራርጦ 42ኛ መዳረሻው በሆነችው ኢትዮጵያ ተገኝቷል፡፡

ከዚህ በፊት ኢትዮጵያን በስም ብቻ ያውቃት እንደነበር ያስታወሰው የሠላም ተጓዡ÷ በአዲስ አበባ በተመለከተው ሁሉ መደነቁን እና መደሰቱን ተናግሯል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ እዚህ መገኘት ልዩ ደስታ ይፈጥራል ያለው ብስክሌተኛው÷ ሕዝቡ እንግዳ ተቀባይ መሆኑንም በተግባር አይቻልሁ ብሏል፡፡

አዲስ አበባ በጥሩ ሁኔታ ተቀብላኛለች፤ እዚህ በመገኘቴም እጅግ ደስተኛ ነኝ በማለት ስሜቱን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አጋርቷል፡፡

ጉዞውን ለማድረግ ምን እንዳነሳሳው ተጠይቆም እንደዚህ ዓይነት ጉዞ ሲያደርግ የመጀመሪያው መሆኑን በማስታወስ÷ “አኅጉር አቀፍ የሠላም ጉዞ ለማድረግ የወሰንኩት በአኅጉሪቱ ሠላም እንዲሰፍን ካለኝ ጥልቅ ፍላጎት የተነሳ ነው” ሲል መልሷል፡፡

ምንም እንኳን ጉዞው አስደሳች ቢሆንም በአንዳንድ ሀገራት ባለው የሠላም ችግር ምክንያት ለማለፍ ተቸግሬ ነበር ሲልም ገልጿል፡፡

በጉዞዬ ባለፍኩባቸው ሀገራት ሁሉ ልክ በሀገሬ እንዳለሁ ይሰማኝ ነበር፤ እኛ አፍሪካዊያን የሚያመሳስለን ነገር የሚበዛ አንድ ሕዝቦች መሆናችንንም ተመልክቻለሁ ብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ቆይታውም ታሪካዊ ቦታዎችን እንደሚጎበኝ ጠቁሞ÷ በቀጣይ ከሥምንት ሀገራት ጉዞ በኋላ ማጠናቀቂያውን በሞሮኮ እንደሚያደርግ አመላክቷል፡፡