አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በውድደሩ የተከተልኩት የሩጫ ስልትና የአሰልጣኝ ድጋፍ ለድል አብቅቶኛል ስትል በግላስጎ የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር የ800 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዋ አትሌት ፅጌ ዱጉማ ተናገረች፡፡
አትሌቷ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረገችው ቆይታ÷ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መነሻውን ያደረገው የአትሌቲክስ ሕይወቷ ወደ ጥሩነሽ ማሰልጠኛ ማዕከል እና በቀጣይም ወደ ክለብ አምርቶ በ200 ሜትር ስትሮጥ እንደነበር ተናግራለች፡፡
በመቀጠል ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተዛወረችው አትሌቷ÷ በ200 ሜትር በሀገር ውስጥ ሻምፒዮናዎች እንዳሸነፈች ነው ያስታወሰችው፡፡
የአቅም ችግር እንደሌለባት እና ጉልበት እንዳላት የምትናገረው አትሌት ፅጌ÷ከ200 ሜትር ይልቅ በ800 ሜትር የመወዳደር ፍላጎት ማሳየቷን ተከትሎ በአሰልጣኟ መልካም ፈቃድ በርቀቱ መወዳደር መጀመሯን ገልጻለች፡፡
ባለፈው ዓመት በቤልጂዬም በተደረገው የዓለም ሻምፒዮና በ800 ሜትር የዓለም አትሌቲክስ መስፈርት የሆነውን ሚኒማ ማምጣቷን የገለፀችው አትሌቷ÷ ሁለተኛ ሰው በመሆን ወደ ስኮትላንድ ግላስጎ ማምራቷን ገልጻለች፡፡
አትሌት ፅጌ በግላስጎው የዓለም የቤት ውስጥ የ800 ሜትር ውድድር ከኬንያውያን አትሌቶች ብርቱ ፉክክር እንደገጠማት አንስታለች፡፡
ይሁን እንጂ ውድድሩን በሰዓት በመከፋፈል የተጠቀመችው የሩጫ ስልት እንድታሸንፍ እንዳገዛት ነው ያስረዳችው፡፡
በውድድሩ አቅም ነበረኝ፤ከፊት ሆኜ ዙሩን መምራት ፈልጌ ነበር፤ነገር ግን በመጨረሻ አቅም እንዳልጨርስ እና ኬንያውያን እንዳይቀድሙኝ አሰብኩኝ፤በመጨረሻም ከኋላ በመስፈንጠር ውድድሩን በቀዳሚነት አጠናቅቄያለሁ ብላለች፡፡
በማሸነፏ ደስተኛ መሆኗን የገለፀችው አትሌት ፅጌ ÷በቀጣይ በዚሁ ርቀት በተለያዩ የዓለም ሻምፒዮናዎች በመሳተፍ የሀገሯን ሰንደቅ አላማ ከፍ ማድረግ እንደምትፈልግ ተናግራለች፡፡