አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኬንያ የአየር ንብረት ለውጥ የምግብ ዋስትናዋ ላይ ትልቅ ስጋት እንደደቀነባት አስታወቀች፡፡
በኬንያ ኤልዶሬት በተዘጋጀው የእርሻ ትርዒት ላይ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ እንደተናገሩት ፥ ተደጋጋሚ ከባድ ዝናብና ደረቃማ የአየር ሁኔታ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ገበሬዎችን በቂ ምግብ እንዳያመርቱ አድርጓቸዋል።
“በቅርቡ የጣለው የኤልኒኖ ዝናብ በእርሻ ላይ ያሉ ሰብሎችን ከማውደም ባለፈ በድህረ ምርት የሚደርሰው ኪሳራ እንዲጨምር አድርጓል” ነው ያሉት፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አርሶ አደሩ መቼ እንደሚዘራ እና እንደሚሰበሰብ ለማወቅ መቸገሩንም አስረድተዋል፡፡
ይህን ተከትሎም መንግሥት አርሶ አደሮች የአየር ንብረት ለውጥ በሚከሰትበት ወቅት ምግብ እንዲያመርቱ የሚያስችላቸውን ዘመናዊ አሠራር እንዲከተሉ እያበረታታ ነው ብለዋል።
ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት ኬንያ እና ሶማሊያን ጨምሮ በቀጣናው ሀገራት ድርቅ መከሰቱ የሚታወስ ነው፡፡
የተከሰተው ድርቅ በኬንያ ከ40 ዓመት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ሲሆን ÷ይህም በ4 ነጥብ 1 ሚሊየንዜጎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የሀገሪቱ ብሔራዊ ድርቅ መከላከል ቢሮ አስታውቋል፡፡
በፈረንጆቹ 2023 ጥቅምት እና ታኅሣሥ ወር በኬንያ በተከሰተው የኤልኒኖ ዝናብ ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች ለህልፈት፣ ለሺህዎች መፈናቀል እና በርካታ ሄክታር ሰብሎችን ለውድመት መዳረጉን ሺንዋ ዘግቧል፡፡
በተያዘው ዓመት ከመጋቢት እስከ ግንቦት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ የተሻሻለ ዝናብ ያገኛሉ ተብሎ ከሚጠበቁ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል ኬንያ አንዷ ስትሆን÷ በዚህም የጎርፍ አደጋ ሊከሰትባት ይችላል ሲል የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ)አስታውቋል።
#Kenya
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!