አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፈረንጆቹ 1916 የተወለዱት ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ አዲስ ዓለም መናገሻ የትውልድ ስፍራቸው ነው፡፡
አባታቸው ገብሩ ደስታ በአውሮፓ የተማሩ ደራሲ እና የአዲስ አበባ የቀድሞ ከንቲባ እና ለአጭር ጊዜም ቢሆን የሴኔት ፕሬዚዳንት የነበሩ ናቸው። እናታቸው ካሳዬ የላምቱ ይባላሉ፡፡
ወይዘሮ ስነዱ ገብሩ በ12 ዓመታቸው ወደ ስዊዘርላንድ ከመላካቸው አስቀድሞ አዲስ አበባ በሚገኘው የስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ከእህታቸው እማሆይ ፀጌ-ማርያም ገብሩ ጋር ቀለም ቀስመዋል፡፡
ወደፈረንሳይ በማቅናትም የዘመናዊ ትምህርቱን (አስኳላ) ከወንዝ አሻገሩት፤ እንግሊዘኛ እና ፈረንሳይኛን ሊያቀላጥፉ ግድ ሆነ፡፡ በዚያም ለስነጽሁፍ ያላቸውን ፍቅር ተረዱ ዲግሪያቸውንም በስዊዘርላንድ ላውሴን ዩኒቨርሲቲ አገኙ፡፡
ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ በፈረንጆቹ 1933 ወደሀገራቸው ኢትዮጵያ በመመለስ በአዲስ አበባ ቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ማስተማር የጀመሩበት ጊዜ ነው፡፡
እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛን መቅሰማቸው ለውጭ ሀገር ጋዜጠኞች በአስተርጓሚነት እንዲያገለግሉም በር ከፈቶላቸውም ነበር፡፡
በልባቸው የስነጽሁፍ ፍቅራቸውን ፈትሸው ካገኙበት ዕለት ጀምሮ ለስነጽሁፍ ጀርባ ላይሰጡ ለራሳቸው ቃል ገቡ።
በዚህ የተነሳም ስነፅሁፍን ለሌሎች አስተምረዋል፤ ከፀሐፌ ተውኔት ዮፍታሄ ንጉሴ ጋር በመሆንም በትምህርት ቤት ተውኔቶችን አዘጋጅተዋል፡፡
ከአንድ ዓመት ትምህርት በኋላ ባለቤታቸው ሎሬንዞ ታእዛዝ የሐረር አስተዳዳሪ ሆነው በመሾማቸው አዲስ አበባን ለቀው ወጡ፡፡
ከ18 ወራት በኋላ ወደ ዋና ከተማዋ ሲመለሱም ባለቤታቸው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ውስጥ የነበራቸው ሚና ለውጥ ሲደረግበትና ጣሊያን ዳግም ወረራ በመበፈጸም እጅ ልታሰጥ ላይ ታች በምትልበት ወቅት ነው፡፡ ባለቤታቸው ወደውጭ ሲያመሩም ከእርሳቸው ጋር መለያየት ግድ ሆነባቸው፡፡
ወይዘሮ ስንዱ በወቅቱ ስለኢትዮጵያ ከሚጽፉ የውጭ ጋዜጠኞች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በመጠቀም የጣሊያንን ወረራ አስመልክተው እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የፖለቲካ ተሳፏቸውን ሀ ብለው ጀመሩ፡፡
ከጊዜ በኋላም ወደኢሉአባቦር በመሄድ የተወሰነ ወታራዊና የህክምና ትምህርትን ቀለም በቃኝ የማይለው ባህሪ ለሆናቸው ለወይዘሮ ስነዱ ገብሩ ግድ ሆነ፡፡ ተማሩ፤ አወቁ፡፡ ጥቁር አንበሶችን ተቀላቀሉ፤ የቀይ መስቀል ክፍልን አቋቋሙ፡፡
ሆኖም በትግል ጊዜያቸው የማይበገሩ ለሀገራቸው የሚሰስቱት አንዳችም ነገር እንዳልነበር ታሪክ ነጋሪዎች ያነሳሉ፡፡ ሆኖም የሳንባ ምች ከያዛቸው በኋላ በጣልያን እጅ ወደቁ፤ ተማረኩ፡፡ በጣልያን ደሴትም ከአባታቸውና ከእህታቸው ጋር ታሰሩ፡፡
ከጊዜ በኋላ ጣልያን ወደሀገሩ በፈረንጆች 1941 መባረሩን ተከትሎ ወደኢትዮጵያ በመመለስ በደሴ የሚገኘው የወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት መምህር ሆኑ። የንጉስ ሚካኤል አሊ የልጅ ልጅ ደጃዝማች አምዴ አሊ ሚካኤልንም አገቡ፡፡
በፈረንጆች 1943 በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሴቶች ትምህርት ቤት ረዳት ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙ ሲሆን፥ ከሁለት ዓመት በኋላ ዋና አስተዳዳሪ ሆኑ፤ ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ሆነ።
ለንጉሱ ልደትም በሴቶች ብቻ የተሰራ ተውኔት ማዘጋጀታቸው ይነገራል፡፡
ለንጉሣዊው ቤተሰብ ሌላ ልደት ከ1947 እስከ 1955፥ 20 ተውኔቶችን ሲጽፉ፥ ተጨማሪ 20 ትርዒቶችን አዘጋጅተዋል።
ከእነዚህ ተውኔቶች መካከል ብዙዎቹ ትግሉን የሚዳስሱ፣ የኢትዮጵያውያንን ጀግንነትና ሰማዕትነት የሚያሳዩ መሆናቸው ይነገራል፡፡
አብዛኞቹ በአማርኛ ተጽፈው ለተውኔት የበቁ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉት በእንግሊዘኛ የተጻፉ ነበሩ፡፡
በፈረንጆቹ 1950 ያሳተሙት ብቸኛው መጽሃፋቸውም ‘’የልቤ መጽኃፍ’’ እንደሆነም ይነገራል፡፡
በፈረንጆች 1957 ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ የመጀመሪያዋ የፓርላማት ተመራጭ ሲሆኑ፤ የተለያዩ የስራ ኃላፊነትን በመውሰድ ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነውም ተሹመዋል፡፡
በ1960 የሴኔት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲሾሙ፥ በ1966 የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ፀሀፊ ሆነው ሰርተዋል፡፡
አይበገሬዋ የጽናት ተምሳሌቷ ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ ከሀገር ወዳድነትና ጀግንነታቸው ባሻገር ለሴቶች መብት የታገሉ ናቸው፡፡
ብዙ ድጋፍ ባያገኙም እና በወቅቱ የፓርላማ አባል ከነበሩት ፊታውራሪ ዘውዴ ኦቴሮ የሚገባቸውን ያክል ባይሆነም ከሌላው በተሻለ ድጋፍ ያደርጉላቸው ነበር ይባላል፡፡
በፓርላማውም ተገኝተው “ዛሬ እኔ ብቻ የሴቶች ተወካይ ልሆን እችላለሁ፤ ሃሳቤንም ከቁብ ላትቆጥሩት ትችሉ ይሆናል ነገር ግን ብዙ ሴቶች በፓርላማ የሚገቡበት ጊዜ ይመጣል እና ለሴቶች መብት መከበር ጠበቃ የሆነው ህግም በሥራ ላይ ይውላል” ማለታቸው ይነሳል፡፡
ወይዘሮ ስንዱ በህይወት ዘመናቸው በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያደርጉ የነበረ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ሴቶች ደህንነት ማህበር፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል እና የመከላከያ ሰራዊት ሚስቶች ማህበር ይጠቀሳሉ፡፡
በአዲስ ዘመን ጋዜጣ “የሴቶች አምድ” ላይ ዘወትር የጽሁፍ አስተዋጽዖ በማበርከት ቀጠሉት የጸሃፊ ተውኔት ጀግናዋ ወይዘሮ ስነዱ ገብሩ፥ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ዘጠኝ ተውኔቶች መስጠታቸው ይነገራል፡፡
በፈረንጆች 2005 ዩኒቨርሲቲው ለሴቶች ላበረከቱት አስተዋጽዖ ክብር ይገባዎታል በሚል የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል፡፡
ልጃቸው አምባሳደር ሳሙኤል አሰፋ (ዶ/ር) በአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም መምህር ሆነው ማገልገላቸው ይታወቃል።
የክብር ዶክተር ስነዱ ገብሩ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ምንጭ ፡- የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን