ጤና

የማር የጤና በረከቶች

By Amele Demsew

March 09, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ንቦች ከእጽዋት አበባ ቀስመው የሚያዘጋጁት የማር ምርት ጣፋጭ ፈሳሽ ሲሆን በዓለም ላይ ተወዳጅ ነው።

በአብዛኛው ወርቃማ ቀለም ያለው ይህ ጣፋጭ የተፈጥሮ ፈሳሽ ለምግብነት እና ለመድኃኒትነት የሚጠቅሙ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ ይዟል።

ማር በንጥረ-ምግቦች እና አንቲኦክሲደንትስ የበለፀገ፣ ፀረ-ባክቴሪያ ባህሪ ያለው ሲሆን በመጠኑ ከወሰድነው የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

ማር በርካታ የጤና ጥቅሞች እንዳሉት ጥናቶች የሚያስረዱ ሲሆን በተለይም በቤት ውስጥ አማራጭ መድሃኒቶችን ለማዘጋጀት በብዛት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡

ስኳር፣ ውሃ፣ ኢንዛይም፣ አሲድ፣ ማዕድናት፣ ቪታሚኖችን፣ አንቲኦክሲዳንቶችን፣ ፕሮቲኖችን፣ ፋይበሮችንና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን በውስጡ ይዟል፡፡

ማር በዋነኛነት ስኳርነት ያለው፣ አነስተኛ መጠን ያላቸው በርካታ ቪታሚኖች እና ማዕድናትን የያዘ እና ለጤና እጅግ ተመራጭ የምግብ አይነት ነው፡፡

ከዋና ዋና የማር የጤና ጥቅሞች መካከል፦ የደም ዝውውርን ማስተካከል፣ የልብ ችግር እንዲሻሻል ማስቻል፣ በቃጠሎ የተጎዳንና የቆሰለ የሰውነት ክፍልን ለማዳን፣ ኮሌስትሮልን ለማመጣጠን፣ ሳል ለማስታገስ፣ ለምግብ መፈጨት እና ሌሎች የጤና ጠቀሜታዎች አሉት፡፡

ማር ከስኳር ይልቅ ለጤና የሚመረጥ በርካታ የጤና ጥቅሞች ያሉት ቢሆንም በመጠኑ ብቻ እንዲወሰድ ይመከራል፡፡

በተጨማሪም ከአንድ አመት በታች እድሜ ላይ ያሉ ህጻናት ማርን መመገብ እንደሌለባቸው ጥናቶች እንደሚያስረዱ የኸልዝ ላይን መረጃ ያመላክታል፡፡