ጤና

ለጤና አገልግሎት ተደራሽነት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወሳኝ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ

By Shambel Mihret

March 07, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎትን በጥራት ተደራሽ ለማድረግ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወሳኝ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው ሀገር አቀፍ የጤና ኢኖቬሽንና ጥራት ጉባኤ ተጠናቋል።

ጉባኤው በኢትዮጵያ የሚሰጠው የጤና አገልግሎት ያለበት ደረጃ፣ ጥራትና ፍትሃዊነት እንዲሁም ደህንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መክሯል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በጉባኤው ማጠቃላያ እንደገለጹት ÷ በኢትዮጵያ ለጤና አገልግሎት መሳለጥ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወሳኝ ነው።

የጤና አገልግሎትን በጥራትና በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ ሀገራዊ ልማቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ የሚያስችል ፖሊሲ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ፖሊሲው በጤናው ዘርፍ ከጤና ሚኒስቴርና ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመስራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸው ፥ ይህም በትብብርና በቅንጅት ለመስራት አጋዥ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት የኢኖቬሽን ሀብ ኃላፊ ሉዜ አገርስናፕ ÷ ሀገራት በዘላቂ ልማት ግቦች በተለይም ጤና ተኮር ግቦች ለማሳካት በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ኢኖቬሽንና አዳዲስ አሰራሮችን መዘርጋት፣ ቅንጅትና ፈጠራ የታከለበት የጤና አገልግሎት መስጠት ይገባልም ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡