Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የዓድዋ ድል በዓል በደቡብ አፍሪካና ፓኪስታን በድምቀት ተከበረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 128ኛው የዓድዋ ድል በዓል በደቡብ አፍሪካ እና ፓኪስታን በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል፡፡

በፕሪቶሪያ ከተማ በተከበረው የዓድዋ ድል በዓል በደቡብ አፍሪካ የተወከሉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበራት ተወካዮች እና ምሁራን ተገኝተዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር (ዶ/ር)÷ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ድል ከመሆኑ ባለፈ ለጥቁር ህዝቦች ምልክት ሆኖ የቆመ ሃውልት ነው ብለዋል፡፡

ድሉ ታሪካዊነቱና ዘመን ተሻጋሪነቱ ለአፍሪካ የነጻነት ትግሎች ፋና ወጊ በመሆኑ እንኮራበታል ሲሉም አውስተዋል፡፡

የበዓሉ የክብር እንግዳ የደቡብ አፍሪካ የማህበራዊ ልማት ሚኒስትር ሊንዲዌ ዙሉ÷ የዓድዋ ድል የአፍሪካውያን የድል ቀንዲል እንዲሁም በአፍሪካና በተለያዩ ቦታዎች ለነፃነት ትግል ያነሳሳ ታላቅ ክስተት ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ 128ኛው የዓድዋ ድል በዓል በፓኪስታን ኢስላማባድ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ በፓኪስታን የቀድሞ ፌዴራል መከላከያ ሚኒስትርና የብሔራዊ ሸንጎ አባል ክሃዋጃ አሲፍ፣ የፓኪስታን የቀድሞ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ሙርታዝ ሶላንጊ፣ የሲንድ ክልል ሀገረ ገዢ ካርማን ቴሶሪ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ሮሚናክ ሁርሲድ እና ሌሎች የሀገሪቱ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም በኢስላማባድ ተቀማጭነታቸውን ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ተገኝተዋል፡፡

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር÷ ኢትዮጵያውያን ነፃነታቸውን ለማስጠበቅ የተቃጣባቸውን የጣልያን ወረራ በመመከት ዓለምን ጉድ ያሰኘ ታላቅ ጀብዱ በዓድዋ ላይ መፈፀማቸውን አውስተዋል፡፡

ዓድዋ የመላ ጥቁር ሕዝቦችን ነጻነት ያበሰረ የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ድል እንደነበር ጠቁመው÷ በመላው ኢትዮጵያውያን ተሳትፎና ተጋድሎ የተገኘ አስተሳሳሪ ድል መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የብሔር፣ የቋንቋ፣ የአካባቢና የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ሳይገድባቸው ቅድመ አያቶቻችንና አባቶቻችን ለጋራ ዓላማ በአንድነት መስዋዕትነት ከፍለው ነፃ ሀገር ለትውልድ ማስረከባቸውን አንስተዋል፡፡

በክብር እንግድነት የተገኙት ክሃዋጃ አሲፍ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት ከመሆኗ በተጨማሪ ወራሪ ሃይልን በመመከት እና ነፃንነቷን በማስከበር ለሰራችው አኩሪ ታሪክ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

Exit mobile version