አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኩላሊት በርካታ ተግባር ያለው አንዱ የሰውነት ክፍል ነው፡፡
ይህ የሰውነት ክፍል ከሚሰራቸው በርካታ ስራዎች ውስጥ በየቀኑ 200 ሊትር ያህል ውሃ ማጣራት፣ ከሰውነት መርዛማ ነገሮች እና አሲድ በሽንት መልክ ማስወገድ፣ የደም ግፊትን መቆጣጠር እንዲሁም የሰውነትን የጨው መጠን መቆጣጠር ይገኙበታል።
እንዲሁም በሰውነት ውስጥ ያለውን ካልሲየምና ፎስፌት በመቆጣጠር የአጥንት ጤንነት የተጠበቀ እንዲሆን ያደርጋል፤ የቀይ የደም ሴል መራባትን ይቆጣጠራል፡፡
የኩላሊት መታወክ ወይም መታመም ደግሞ በሰውነት ውስጥ ያሉ መርዛማ ነገሮች እና አሲድ በሽንት አማካኝነት ባለመወገዳቸው መታፈንን እና ለመተንፈስ መቸገርን ያመጣል ለደም ግፊት ሕመምም ያጋልጣል፡፡
በተጨማሪም ሰውነት ቀይ የደም ሴልን በተገቢው መጠን እንዳያመርት ከማድረጉም በላይ አጥንት ጥንካሬ ያጣል፣ እንደተፈለገው መንቀሳቀስ እንዳይቻል እንደሚያደርግም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚህም በተለይ የስኳር ታማሚዎች፣ ከፍተኛ ደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች፣ ወፍራም ሰዎች፣ በቤተሰባቸው የኩላሊት፣ የስኳር፣ የከፍተኛ የደም ግፊት ሕመም ያለባቸው ሰዎች ምርመራ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
የደም ግፊትን በማስተካከል፣ በምግብ ላይ ጨው በመቀነስ፣ ስኳርንና ቅባትን (ኮሊስትሮል) በማስተካከል፣ ሲጋራ ባለማጨስ፣ ስፖርት በመስራት እና የሰውነት ክብደትን በማስተካከል ከኩላሊት በሽታ መጠበቅ እንደሚቻል የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡