Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በፍትሕ ዘርፉ የሽግግር ፍትሕና የፍትሕ መዋቅራዊ ለውጥ ፍኖተ ካርታ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፍትህ ዘርፉ የሽግግር ፍትሕና የፍትሕ ስርዓት መዋቅራዊ ለውጥ ፍኖተ ካርታ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴርን የ2016 ሁለተኛው ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፤ በሚኒስቴሩ ከፍትህ አኳያ በዋነኝነት የጸጥታ ጉዳይና የፍትህ ዘርፍ ማሻሻያ ጉዳዮች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡፡

በዚህም ጸጥታውን በሚመለከት ኢትዮጵያ ሽግግር ውስጥ እንደመሆኗ የሽግግር ፍትህን መከተል ተገቢ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው÷ በተለያዩ የመንግስት አስተዳደሮች ሲሰራባቸው የቆዩ የፍትህ ዘርፍ ማሻሻያዎች ጥንካሬና ድክመትን በመለየት አዲስ የፍትሕ መዋቅራዊ ለውጥ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በፍኖተ ካርታው ላይ ከክልሎች ጋር በመወያየት ወደተግባር እየተገባ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአንዳንድ ክልሎች ላይ ተተግብሮ ለውጥ ማሳየት መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡

መዋቅራዊ ለውጥ ፍኖተ ካርታው 10 የትኩረት አቅጣጫዎች ያሉት ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በበጀት አመቱ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራበት የታሰበው ማህበረሰብ ተኮር የፍትህ አገልግሎት መሆኑን ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የመዋቅራዊ ለውጡና የሽግግር ፍትህ ፍኖተ ካርታና ፖሊሲ ትግበራ በፍትህ ዘርፉ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ግጭትን የመከላከልና የመፍታት አቅምን ማዳበር ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች መኖራቸውን አብራርተዋል።

አሁን ላይ ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት ከህግ ማስከበር ስራው ጎን ለጎን ከማህበረሰቡ ጋር መወያየትና በግጭቱ ከሚሳተፉ ወገኖችም ጋር ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማግኘት የተጀመሩ ስራዎች እንዳሉም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው

Exit mobile version