አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም ዓቀፍ ነዳጅ ላኪ ሀገራት የነዳጅ ገበያ ፍላጎት ተለዋዋጭነትን በመቅረፍ ምቹ የገበያ እድል ለመፍጠር በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ተሰምቷል፡፡
“የተፈጥሮ ጋዝ ለአስተማማኝ እና ቀጣይነት ያለው የወደፊት ዕጣ ፈንታ” በሚል መሪ ሀሳብ በአልጄሪያ በተካሄደው 7ኛው የሀገራቱ ጉባኤ 14 ሀገራት የነዳጅ ገበያ ፍላጎት ተለዋዋጭነት ለማስቀረት የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸው ነው የተገለጸው፡፡
ስምምነት ላይ ከደረሱት ሀገራት ውስጥ ሩሲያ፣ ኢራን፣ ኳታርና ቬንዙዌላ እንደሚገኙበትም ተጠቁሟል።
በጉባኤው የሀገራቱ ተወካዮች በየጊዜው የሚፈጠረው የተፈጥሮ ጋዝ ፍላጎት ተለዋዋጭነት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑ እንዳሳሰባቸው መግለጻቸውን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በተጨማሪም÷ የኢንዱስትሪዎች በነዳጅና በተፈጥሮ ጋዝ ላይ ያሳዩት መቀዛቀዝና አዳዲስ ታዳሽ የኃይል ምንጮች ላይ እያሳዩት ያለው የፍላጎት መጨመርም በጉባኤው ትኩረት ተሰጥቶታል።