ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ በጋዛ ለተደቀነው የረሃብ አደጋ ድጋፍ እንዲደርስ እስራኤል እንድትተባበር አሳሰበች

By Meseret Awoke

March 04, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋዛ የደረሰውን ረሃብ ተከትሎ እስራኤል ወደ አካባቢው ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደርስ ትብብር እንድታደርግ አሜሪካ አሳስባለች፡፡

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ በጋዛ ያሉ ዜጎች እየተራቡ ነው ያሉ ሲሆን ፥ በዚህም በአካባቢው ተጨማሪ ድጋፎች እንዲደረጉ እስራኤል አስፈላጊውን ትብብር እንድታደርግ አሳስበዋል፡፡

ለዚህም ቢያንስ ለሚቀጥሉት ስድስት ሣምንታት የተኩስ አቁም ስምምነት ሊደረግ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡

እስራኤል ከሰዓታት በፊት በግብጽ ካይሮ ይካሄዳል ለተባለው የተኩስ አቁም ድርድር አለመገኘቷ የተነገረ ሲሆን ፥ ለዚህም ሃማስ በሕይዎት ያሉ ታጋቾችን ስም ዝርዝር እየሰጠ አይደለም የሚል ምክንያት ማቅረቧ ተመላክቷል፡፡

የሃማስ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ባሴም ናይም(ዶ/ር) በበኩላቸው÷ “እስራኤል የቦምብ ጥቃት እየፈጸመች ባለችበት ሁኔታ ማን በሕይወት እንዳለ ማወቅ አይቻልም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በሌላ በኩል የሃማስ ልዑካን ቡድን፣ የአሜሪካ እና የኳታር አደራዳሪዎች በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ይካሄዳል ተብሎ ለታቀደው ድርድር ተገኝተዋል፡፡

እሑድ በአላባማ በተደረገ አንድ ዝግጅት ላይ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ እንደተናገሩት ፥ በጋዛ ሰዎች የሚመገቡት ነገር የላቸውም ፤ ሴቶች የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸውን ሕፃናት እየወለዱ ነው ፤ በተመጣጠነ ምግብ እጥረትና በድርቀት ምክንያት ሕጻናት ሕይወታቸውን እያጡ ይገኛሉ፡፡

ችግሩን ለመቀነስም የተኩስ አቁም ይደረግ ፤ ታጋቾችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እናገናኝ ፤ ለጋዛ ሕዝብ አፋጣኝ ድጋፍ እናድርግ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለዚህ ተግባራዊነት ሁለቱም ወገኖች የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ሊያደርጉ እንደሚገባ ማሳሰባቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

#Gaza #Israel #America #Hamas

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!