Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በግላስጎ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንደኛ በመሆን አጠናቀቀች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ደግሞ አምስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቅቃለች።

19ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በፈረንጆቹ ከመጋቢት 1 እስከ 3 ቀን በስኮትላንዷ መዲና ግላስጎ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን÷ በሻምፒዮናው ከ130 በላይ ሀገራት የተወጣጡ ከ650 በላይ አትሌቶቸ ተሳትፈዋል ።

ኢትዮጵያ በ800 ሜትር፣ በ1 ሺህ 500 ሜትር እና በ3000 ሜትር በሴትና በወንድ በአጠቃላይ በ8 ሴቶች እና በ5 ወንዶች በድምሩ በ13 አትሌቶች ተሳትፋለች ፡፡

በሴቶች 800 ሜትር ፅጌ ዱጉማ እና በሴቶች 1 ሺህ 500 ሜትር ፍሬወይኒ ሃይሉ የወርቅ፣ በሴቶች 3000 ሜትር ጉዳፍ ፀጋዬ የብር እንዲሁም በወንዶች 3000 ሜትር ሰለሞን ባረጋ የነሃስ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ ሁለት ወርቅ፣ አንድ ነሃስ እና አንድ ብር በአጠቃላይ አራት ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች፡፡

ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያ ውድድሩን ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም ደግሞ 5ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቋን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version