ጤና

ጥቂት ስለታይሮይድ ህመም

By Meseret Awoke

March 04, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ታይሮይድ በሰውነትዎ ውስጥ በተለያዩ ስርዓቶች ውስጥ ሚና የሚጫወቱ ሆርሞኖችን ያመነጫል።

ከአስፈላጊ ሆርሞኖች ውስጥ በዝቶ ወይም አንሶ ሲመነጭ የታይሮይድ በሽታ ተብሎ ይጠራል፡፡

ሃይፐርታይሮይዲዝም፣ ሃይፖታይሮዲዝም፣ ታይሮዳይተስ እና ሃሺሞቶ ታይሮዳይተስን ጨምሮ የተለያዩ የታይሮይድ በሽታ ዓይነቶች አሉ።

ታይሮይድ ሜታቦሊዝምን የሚቆጣጠሩ የታይሮይድ ሆርሞኖችን (ቲ3 እና ቲ4) በመልቀቅ እና በመቆጣጠር በሰውነት ውስጥ የሚያከናውናቸው የተለያዩ ስራዎች እንዳሉት ይነሳል፡፡

ሜታቦሊዝም ምግብ ወደ ጉልበት የሚቀየርበት ሂደት ሲሆን ፥ ብዙ የሰውነት ሥርዓቶች በትክክል እንዲሠሩ ለማድረግ ይህ ኃይል በመላ ሰውነት ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላል።

ታይሮይድ በትክክል ሲሰራ፣ ሜታቦሊዝም በትክክለኛው መጠን እንዲሰራ ትክክለኛውን የሆርሞን መጠን የሚይዝ ሲሆን ፥ ሆርሞኖች ጥቅም ላይ በሚውሉበት ጊዜ፣ ታይሮይድ ተተኪዎችን እንደሚፈጥርም ነው የሚነገረው፡፡

የታይሮይድ በሽታ የታይሮይድ ሆርሞኖችን (ቲ3 እና ቲ4) ሲያንሱ ወይም ሲበዙ የሚፈጠር ሲሆን ፥ የታይሮይድ ሆርሞን ሲበዛ የሰውነት ሜታቦሊዝም ሂደት ስለሚፈጥን የልብ ምት መጨመር ፣ ክብደት መቀነስና የድካም ስሜትን ይፈጥራል፡፡

በተጨማሪም የወር አበባ መዛባት እና ሙቀት መቋቋም አለመቻል ምልክቶቹ ሲሆኑ ፥ የታይሮይድ ሆርሞኖች ሲያንስ ደግሞ የእነዚህን ምልክቶች ተቃራኒ እንደሚሆን ከአዲስ አበባ፣ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡