አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል የወል አብሮነትን በጽኑ መሠረት ላይ ያኖረ ነው ሲሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡
‹‹ዓድዋ የመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራት›› በሚል መሪ ሐሳብ 128ኛው የዓድዋ ድል በዓል ፒያሳ በሚገኘው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ተከብሯል፡፡
አፈ-ጉባዔ አገኘሁ በአከባበሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የዘንድሮው በዓል ድሉን በሚመጥነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል፡፡
አባቶቻችን ሀገራችንን ከጠላት ለመጠበቅ ተዋድቀው በኩራት እንድንኖር አድርገውናል ያሉት አፈ-ጉባዔው÷ የቅኝ ገዥዎችን ሕልምም ማምከን የቻሉት ተደማምጠው በአንድነት በመሰለፋቸው ነው ብለዋል፡፡
እኛም አብሮነት እና የጋራ ራዕይ ሊኖረን ይገባል የምንለው የዓድዋ ልጆች ስለሆንን ነው ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድልም ዘመናትን የመሻገሩ ምስጢር የሰውን ልጅ እኩልነት የገለጸ፣ አንድነትን ያጎላ እና እውነትን ያሳየ በመሆኑ ነው ብለዋል በንግግራቸው፡፡
የወል አብሮነትን በጽኑ መሠረት ላይ ያኖረ እና ጉልኅ ታሪክ የጻፈ በዓል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከ128 ዓታት በኋላ ድሉን የሚመጥን መታሰቢያ ዕውን እንዲሆን ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችም÷ ከዓድዋ ድል ሕዝባዊ ፍቅርን፣ ወንድማማችነትን፣ እህትማማችነትን ልንማር ይገባል ብለዋል፡፡
ሁሉም ዜጋ በነጻነት የሚኖርባት የበለጸገች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደትም ሕዝቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ከመቼውም ጊዜ በላይ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የዓድዋ ድል በዓልን ስናከብር÷ በእኩልነት፣ በአብሮነት፣ በፍቅር እና በመተሳሰብ ሊሆን እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡