የሀገር ውስጥ ዜና

ምክክር ኮሚሽኑ ከወላይታ ዞን የሚሳተፉ ተወካዮችን መረጣ አጠናቀቀ

By Amele Demsew

March 01, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከወላይታ ዞን በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የማህብረሰብ ተወካዮችን መረጣ አጠናቅቋል፡፡

ከየካቲት 19 እስከ የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም በወላይታ ዞን ከ23 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ከተውጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚቀርቡትን አጀንዳዎች ለማሰባሰብ 600 ተወካዮችን በማስመረጥ መጠናቀቁን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በተወካዮች መረጣ ላይም ሴቶች፣ ወጣቶች፣የንግዱ ማህበረሰብ፣ መምህራን፣ አርሶ አደሮች እና ሌሎች የማሕበረሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውንም ገልፀዋል ፡፡

የተወካዮች መረጣው አካታች፣ ግልጽ፣ አሳታፊና እና ተዓማኒ እንደነበርና በምርጫ ሂደትም ከእያንዳንዱ የማሕበረሰብ ክፍል ሁለት ተወካዮች ከአንድ ተጠባባቂ ጋር እንደተመረጠም ተመላክቷል፡፡

በማስተዋል አሰፋ