አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አትሌት ወንድወሰን ከተማ አበረታች መድኃኒት በመጠቀሙ የአራት ዓመት እገዳ እንደጣለበት የብሔራዊ ፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
ጽህፈት ቤቱ አትሌት ወንድወሰን ከተማ ማሞ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ታኅሣሥ 1/2019 በቻይና ሻንዚቢ ዓለም አቀፍ የግል ማራቶን ውድድር ላይ በስፖርት የተከለከለ አበረታች መድኃኒት (ዶፒንግ) መጠቀሙን በመረጋገጡ ለአራት ዓመታት የእግድ ቅጣት ተጥሎበታል ብሏል።
አትሌቱ በማንኛውም አገር አቀፍ ይሁን ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዳይሳተፍ ነው ቅጣቱ የተጣለበት።
በዚህ ውድድር ላይ ብቻ ያስመዘገበው ውጤትና ሽልማት እንዲሰረዝ ዉሳኔ መተላለፉን የፀረ አበረታች ቅመሞች ጽህፈትቤት አስታውቋል።
በተጨማሪም ሁለት አትሌቶች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በግላቸው በተሳተፉባቸው ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን መጠቀማቸው ጥርጣሬ በመኖሩ ጉዳያቸው በመጣራት ላይ መሆኑን ተገልጿል።
የሁለቱ አትሌቶች ዉሳኔው እንደተጠናቀቀም ቅጣቱንና ሥም ዝርዝራቸው ይፋ እንደሚሆነም ተጠቅሷል።
ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ስፖርታዊ ውድድሮች ለጊዜው ቢቋረጥም የስፖርት አበረታች ቅመሞች ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።