የሀገር ውስጥ ዜና

የዲጂታል አሰራሮችን በመዘርጋት አገልግሎቶችን ቀላልና ቀልጣፋ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተመላከተ

By Amele Demsew

February 29, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዲጂታል አሰራሮችን በመዘርጋት የመንግስት አገልግሎቶችን ቀላልና ቀልጣፋ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የጀርመን ተራድኦ ድርጅት በኢንቨስትመንት እና ቢዝነስ ከባቢ ሁኔታ ፕሮጀክት ላይ ያዘጋጁት የዲጂታል ኢትዮጵያ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ኮንፈረንሱ የኢትዮጵያን የእስካሁን እና የቀጣይ የዲጂታል ጉዞ የሚመለከቱ ጉዳዮች የቀረቡበት መሆኑ ተመላክቷል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር)÷ የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ እውን ለማድረግ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና አጋሮች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ ዲጂታል አሰራሮችን በመዘርጋት የመንግስት አገልግሎቶችን ቀላልና ቀልጣፋ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአውሮፓ ህብረት በዚህ ረገድ እያደረገ ስላለው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በንግድ ስራ ቅልጥፍና እና በኤሌክትሮኒክ መንግስት ስትራቴጂ ዝግጅት ላይ ህብረቱ ድጋፍ እያደረገ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የህብረቱ የምጣኔ ሃብት አስተዳደር ቡድን መሪ ኢዮዋና አልበሊስኩ በበኩላቸው÷ የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የዲጂታል ጉዞ እውን መሆን እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡