የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራና ትግራይ ክልሎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የአትክልትና ፍራፍሬ ዘር ድጋፍ ተደረገ

By Shambel Mihret

February 27, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የአትክልትና ፍራፍሬ ዘር ድጋፍ ተደርጓል፡፡

ቢኤኤስኤፍ ከኔዘርላንድ የልማት ድርጅት ጋር ሆርቲ-ላይፍ በተሰኘው ፕሮጀክት በግጭት እና በድርቅ ለተጎዱ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ለሚገኙ 4 ሺህ አርሶ አደሮች የሚከፋፈል የአትክልትና ፍራፍሬ ዘር ነው ድጋፍ ያደረጉት፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር) በወቅቱ እደገለጹት÷ ድጋፉ በግጭትና ድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋምና የአርሶ አደሩን ህይወት ለመደገፍ ያለመ ነው።

ድጋፉ የቀይ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ቃሪያና ሀብሀብ ዘርን ያካተተ ነውም ማለታቸውን ከአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተደረገው ድጋፍም 371 ሄክታር መሬት ማልማት እንደሚቻል ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

የኔዘርላንድስ የልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጁሊ ግርሃም በበኩላቸው÷ ድርጅቱ የአርሶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻል የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከዘር ድጋፍ ባለፈም አጠቃላይ የአትክልትና ፍራፍሬ አመራረት ስልጠናዎችም እንደሚሰጡ ተናግረዋል።