Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አቶ አሕመድ ሺዴ የአፍሪካ ልማት ባንክ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲያደርግ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ልማት ባንክ በቀጣይ ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ጠንካራ ትብብር እና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲያደርግ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ ጠየቁ፡፡

አቶ አሕመድ በአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ዋና ዳይሬክተር ጆናታን ንዛይኮሬራ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ባንኩ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም አኅጉራዊ ፕሮጀክቶችን በማስተባበር ብሎም የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭን በመደገፍ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ሚኒስትሩ አድንቀዋል፡፡

በፋይናንሱ ዘርፍ እየተሠሩ ላሉ የማሻሻያና የአቅም ግንባታ ሥራዎችም ባንኩ እያደረገ ስላለው የቴክኒክ ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

በቀጣይ ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶችም ጠንካራ ትብብር እና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲያደርግ አቶ አሕመድ ጠይቀዋል።

ጆናታን ንዛይኮሬራ በበኩላቸው÷ ባንኩ ለኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት፣ የውኃ፣ የግብርናና የአግሮ ኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ለተለያዩ ተቋማት ስለሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ ድጋፎች አብራርተዋል፡፡

ለመንግሥትና ለግል ተቋማት ባንኩ በቀጣይ ስለሚያደርጋቸው ድጋፎችም ገለጻ ማድረጋቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያና በአጠቃላይ በቀጣናው ቀጣይነት ያለው ልማት እንዲጎለብትና በሁሉም ጉዳዮች ጠንካራ ትብብር እና ወቅታዊ ውይይት ለማድረግ የግንኙነት ጊዜ እንዲኖራቸው ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

Exit mobile version