የሀገር ውስጥ ዜና

የምስራቅ አፍሪካ የሚኒስትሮች የፍልሰት ጉዳዮች ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

By Amele Demsew

February 26, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አምስተኛው የምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የሚኒስትሮች ቀጣናዊ የፍልሰት ጉዳዮች ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ አስር የቀጣናው አባል ሀገራት፣ የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስትታት ድርጅት (ኢጋድ) እና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛል።

መድረኩ በቀጣናው አባል ሀገራት መካከል የሚስተዋለውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፍልሰተኞች ቁጥር ለመቆጣጠር በፖሊሲ የተደገፈ ምክረ ሃሳብ ለማስቀመጥ የሚያስችል መሆኑ ታውቋል።

በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሰፊ የፍልሰተኞች ቁጥር ያላቸውና መተላለፊያ የሆኑ ሀገራት፤ በዘርፉ የአስተዳደር ስልቶችን የተመለከተ የልምድ ልውውጥ በማድረግ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ተገልጿል።

ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት በሚዘልቀው የምክክር መድረክ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሶማሊያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን፣ የኡጋንዳ፣ የሩዋንዳ፣ የታንዛኒያ፣ የብሩንዲ፣ የኤርትራና የጅቡቲ ተወካዮች እየተሳተፉ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡