የሀገር ውስጥ ዜና

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ታሪክን ለትውልድ በማሸጋገር ረገድ ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ተገለጸ

By Shambel Mihret

February 22, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል መታሰቢያ ታሪክን ለቀጣይ ትውልድ በማሸጋገር ረገድ ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ፡፡

የአገልግሎቱ ከፍተኛ አመራሮች የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝተዋል፡፡

የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀኔራል ሲሳይ ቶላ በወቅቱ÷የአድዋ ድልን የሚመጥን መታሰቢያ መገንባቱ የኢትዮጵያውያን የጋራ ዕሴት የሆኑትን ነፃነትን ያለማስደፈር እንዲሁም የአንድነት መንፈስን ለትውልድ በማሸጋገር ረገድ ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለነፃነታችንና ለአንድነታችን የተከፈለውን መስዋዕትነት ከመዘከር ባለፈ የአሁኑ ትውልድ እያከናወናቸው ያሉ ለመጪው ትውልድ የሚሸጋገሩ ስራዎችንም አስተሳስሮ መያዙ ትርጉም እንዳለው አብራርተዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀኔራል ርስቱ ይርዳ በበኩላቸው÷የአድዋን ታሪክ በአንድ ቦታ አሰባስቦ ለማስተማርና ለትውልዱም ለማሸጋገር በሚያመች መንገድ መታሰቢያው መገንባቱ የሚያኮራ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ስንሰባሰብ ታሪክ መስራት እንደምንችል፣ የሚያሰባስቡን ታላላቅ ጉዳዮች እንዳሉንም ምሳሌ እንደሚሆን አንስተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጉብኝት መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው እንደገለፁት÷ፕሮጀክቱ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የታሪክ ቅብብሎሽ እንዲኖር ታልሞ የተተገበረ ነው፡፡