አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቡድን 20 ሀገራት ጉባኤ ላይ ብራዚል በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ውክልና ለማግኘት ጥረት እንደምታደርግ አስታወቀች፡፡
የቡድን 20 ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሪዮ ዲጄኔሮ ፥ ድህነት፣ የአየር ንብረት ቀውስ እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ችግሮች ላይ መክረዋል።
የሕብረቱን ዓመታዊ የፕሬዚዳንትነት ቦታ የተረከበችው ብራዚል ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮችንም አስቀምጣለች።
ይህም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በዓለምአቀፍ የአስተዳደር ተቋማት እና በባለብዙ ወገን ባንኮች በአግባቡ ውክልና እንዲኖራቸው ለማድረግ ግፊት ያደረገ እንደሆነም ነው የተገለጸው።
በብራዚል የሚመራው ጂ20 ጉባኤ በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ተብሏል።
እነዚህም ረሃብን፣ ድህነትን እና አድሎአዊነት መዋጋት፤ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በአካባቢ ገጽታ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ እንዲሁም በዓለምአቀፍ አስተዳደር ላይ ስለሚደረግ ማሻሻያ ናቸው፡፡
የከፍተኛ ዲፕሎማቶች ስብሰባ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ግጭቶች እየተስፋፉ መምጣታቸውን ተከትሎ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
ይህም ዓለም ለልማትና ለድጋፍ ማዋል ያለባትን ከ2 ትሪሊየን ዶላር በላይ በዓመት ለወታደራዊ በጀት እንደሚውልም የብራዚል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቬራ ተናግረዋል፡፡
አክለውም ፥ ብራዚል የዓለም ሰላም እና ደህንነት እንዳሳሰባት ገልጻ ፥ በዓለም ላይ ከ170 በላይ ግጭቶችን በማስመዝገብ ትልቁን ሪከርድ እንደተመዘገበ ግምቶች እንዳሉም ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች እየጨመሩ መምጣታቸውንም ነው ያመላከቱት።
በፈረንጆች 2024፣ ከሕዳር 18 እስከ 19 በሪዮ ዲጄኔሮ ከሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ቀደም ብሎ የ20ዎቹ መሪ የበለጸጉ ሀገራት ተወካዮች የስራ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ለሁለት ቀናት ይቆያሉ ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የገንዘብ ሚኒስትሮች እና የማዕከላዊ ባንክ ፕሬዚዳንቶች በሚቀጥለው ሣምንት በሳኦ ፓውሎ እንደሚገናኙ አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።
ባለፈው ረቡዕ የብራዚል ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ጋር በዋና ከተማዋ ብራዚሊያ ለሁለት ሰዓታት ያህል በዓለም አቀፍ አስተዳደርና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።