አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሬጌው ንጉስ ሮበርት ነስታ ማርሌይ በመድረክ ስሙ ቦብ ማርሌይ የሕይወት ታሪክ ላይ የተመሰረተው ፊልም በተለያዩ የአሜሪካ ሲኒማ ቤቶች በመታየት ላይ ይገኛል፡፡
ቦብ ማርሌይ፥ ሬጌን፣ ስካ እና ሮክስቴዲይ የተባሉ የሙዚቃ ዓይነቶችን በማዋሃድ በልዩ ድምጽና የዘፈን አጻጻፍ ስልቱ ታዋቂነትን ያተረፈ ነው፡፡
ለሙዚቃ ያበረከተው አስተዋፅዖ የጃማይካ ሙዚቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነቱ እንዲጨምር ማድረጉ የማያጠያይቅ ነው ይላሉ የሙዚቃ ሊቆች፡፡
ቦብ ማርሌይ የጃማይካ ሙዚቃ እና ባህል እንዲሁም ማንነት ዓለም አቀፋዊ ምልክት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ሬጌን ሲነሳ ቦብ ማርሌይ፤ ቦብ ማርሌይ ሲነሳ ሬጌ ይነሳል።
ከሙዚቀኛነቱ ባሻገር በነጻነት ታጋይነቱም የሚታወቀው ጃማይካዊው የሬጌ ንጉስ፣ የነጻነት ሰባኪው፣ የፍቅር አቀንቃኙ ቦብ ማርሌይ፤ ለሰው ልጆች ሰላምን ለመስበክ ድምጹንና የሚያገኛቸውን መድረኮች በአግባቡ ተጠቅሞ ያለፈ እንደሆነ ዓለም ይመሰክርለታል።
የፓን አፍሪካ አቀንቃኙ የሬጌው ምልክት፥ ቤቱ ለሆነችው አፍሪካና ህዝቦቿ ነጻነት በጽኑ ታግሏል።
‘’አፍሪካ ዩናይት‘’ የሚል ሙዚቃውም ለአህጉሪቱም ሆነ ለመላው የጥቁር ህዝብ ተስፋቸውን የሚያለመልም ዝማሬ ነው፡፡
ቦብ ማርሌይ ‘መንፈሳዊ ቤቴ ናት’ የሚላት ኢትዮጵያ ደግሞ ለእሱ ትለያለች፤ ሰንደቅ ዓላማ ማጌጫው ብቻ ሳይሆን ምልክቱ ነው፡፡
በሙዚቃ ሕይወቱ 13 የስቱዲዮ አልበሞችን፣ 133 ነጠላ ዜማዎች፣ 38 ‘’ኮምፓይሌሽን‘’ አልበም እንዲሁም ከኮንሰርት ቀጥታ ስርጭት የተቀዱ 6 አልበሞችን ለአድማጭ አበርክቷል፡፡
ቦብ ማርሌይ ስለዓለም ሰላም ድምጹ አይሰንፍም ፤ የጊታሩ ክሮች አይላሉም፡፡
ሙዚቃዎቹ ነጻነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ እኩልነት፣ ምኞት፣ መልካምነት፣ እርቅ ናቸው፤ በሙዚቃዎቹ በኩል ያስተምራል፡፡
ይህን አስመልክቶም ‘ዋን ላቭ’ በሚል ርዕስ ሙዚቃዊ ድራማ ፊልም ተሰርቶ በዚህ ወር ለእይታ የበቃ ሲሆን፥ ሬናልዶ ማርከስ ግሪን በአዘጋጅነት ተሳትፎበታል፡፡
ፊልሙ የሬጌው አቀንቃኝ እና የሙዚቃ ጽሁፍ ጥበበኛው ቦብ ማርሌይ ወደታወቂነት ከመጣበት የፈረንጆቹ 1970ዎቹ ጀምሮ ህይወቱ እስካለፈበት በፈረንጆቹ 1981 ድረስ ያለውን ጉዞውን የሚያስቃኝ ነው ተብሏል፡፡
ፊልሙ ለዕይታ በቀረበ በቀናት ውስጥ ከፍተኛ ገቢ ማስገባቱና በዓለም የፊልም ሰንጠረዥ በሣምንት 29 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም በአጠቃላይ 54 ሚሊየን ዶላር በማስገባት አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
የ11 ልጆች አባት የነበረው ቦብ ማርሌይ፥ አብዛኞቹ ልጆቹ እና የልጅ ልጆቹ በሙዚቃው (በሬጌ) ዓለም ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ለዓለም ላደረገው አበርክቶም የተለያዩ ከፍተኛ ዓለም አቀፋዊ ሽልማቶችን አግኝቷል።