ቴክ

በሞባይል ባንኪንግ አማካኝነት የሚፈጸሙ ማጭበርበሮችን መከላከያ መንገዶች

By Meseret Awoke

February 22, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገራችን ያለው የፋይናስ ስርዓት መዘመን ጋር ተያይዞ ባንኮች እና የፋይናስ ተቋማት ደንበኞቻቸው የተለያዩ የዲጂታል የባንኪንግ ስርአቶችን እንዲጠቀሙ ያበረታታሉ፡፡

ከነዚህም ውስጥ የሞባይል ባንኪንግ ስርአት በዋናነት ይጠቀሳል፤ የዚህ አገልግሎት ተቃሚዎች ቁጥር የመበራከቱን ያህል የሚከሰቱ ማጭበርበሮች ቁጥርም እያደገ ይገኛል፡፡

በመሆኑም የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ሊደርስባቸው ከሚችል ማጭበርበሮችና ውንብድና ራሳቸውን ለመከላከል የሚከተሉትን የጥንቃቄ መንገዶች ተግባራዊ ማድረግ ይገባቸዋል፡- ● ሞባይላችን/የመገልገያ መሳሪያችንን/ መቆለፍ – በተለይም ግብይቶች ስንፈጽምም ይሁን በማንኛውም ጊዜ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ መያዝ፤ በጠንካራ የይለፍ ቃል ወይም በባዮሜትሪክ አማራጮች መቆለፍ፣ ● ግብይቶችን /ክፍያዎች/ ስንጨርስ ከክፍያ መተግበርያዎች/ዌብሳይቶች (Web Pages) ዘግተን በመውጣት የይለፍ ቃሎች የተቆለፉ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ ● የባንክ ሒሳቦቻችን ሁኔታ መግለጫ (Statements) በየግዜው መፈትሽ/መመልከት፣ ● ማንኛውን የሞባይል ባንኪንግ ግብይቶች በነፃ ዋይፋይ አለመፈፀም፤ ሁሌም ሞባይል ዳታ መጠቀም፣ ● ባለ ሁለት/ባለብዙ ደርዝ ማረጋገጫ /Two-factor or Multi-factor Authentication / ተግባራዊ ማድረግ፤ ወደ ባንክ ሒሳብዎ ከመግባትዎ በፊት የአንድ ግዜ ይለፍ ቃል /SMS OTP/ ወደ ስልክዎ ወይም የኢሜይል አድራሻ እንዲላክ ማድረግ፣ ● የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያዎቻችን ማዘመን፡- የሞባይል ባንኪንግ ይሁኑ ሌሎች ሞባይላችን ውስጥ የምንጭናቸው መተግበርያዎች ወቅታዊ ዝማኔዎች ማድረግ እንዲሁም ከታማኝ ምንጮች አውርዶ መጠቀም፤ ካልሆነ ሚስጥራዊነት ያላቸውን መረጃዎች ለመመንተፍ ሊያመቻቹ ይችላሉ፣ ● በባንክ ድረ –ገፆች ላይ የተቀመጡ የደህንነት መመርያዎችን መከተልና መተግበር፣ ● ሞባይላችንን ላለመጠቀም ወይም ለሌላ ሰው ለመስጠት ስንወስን የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያውን እና ታሪኩን ማስወገድ እና ሚስጥራዊ መረጃዎችን ማጥፋት፣ ● ወደ የሞባይል ባንክ አካውንታችን ከመግባታችን በፊት ውጤታማ እና የዘመነ ጸረ-ቫይረስ/አንቲስፓይዌር ሶፍትዌር እና ፋየርዎል እንዳለን ማረጋገጥ፣ ● አሳሾችን በመደበኛነት ማፅዳት – አንዳንድ ሞባይል ስልኮች እና ታብሌቶች የባንክ መረጃዎን ሊይዙ የሚችሉ የድረ-ገጾች ቅጂዎችን ያከማቻሉ ይህን አለመፍቀድ፣ ● የሞባይል ደህንነትን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያዳክም እና ለማጭበርበር ሊያጋልጥ የሚችል የባንኪንግ አገልግሎት አለመጠቀም፣ ● ስልካችንን ለመክፈት እና የባንክ መተግበሪያዎችን ለመክፈት የተለያዩ የፒን ቁጥሮችን (የይለፍ ቃል) መጠቀም፣ ● የሞባይል ባንኪንግ የይለፍ ቃሎች ወይም ፒኖች በስልክ ላይ ሴቭ አድርጎ አለማስቀመጥ፣ ● ሀሰተኛ የክፍያ ማረጋገጫ የጽሑፍ መልዕክቶችን መጠንቀቅ – የሽያጭ ክፍያ በሚፈፀምበት ግዜ ገንዘቡ ወደ ባንክ ሒሳባችን በትክክል መግባቱ/አለመግባቱ ወደ ባንክ ሂሳባችን በመግባት ማረጋገጥ፣ ● ክፍያ እንደተፈፀመ በማስመሰል ተመሳስለው የተሰሩ መልእክቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ መጠንቀቅ፤ ለምሳሌ ሰዎች እቃ ከኛ ሲገዙ ክፍያው በባንክ/ሞባይል ክፍያ መንገድ እንደከፈሉ በማስመሰል የእነዚህ የክፍያ ማረጋገጫ መልእክቶችን በማስመሰል ለማጭበርበር ሊሞክሩ ይችላሉ በመሆኑም መልዕክቶቹ ትክክለኛ መሆናቸዉን ማረጋገጥ፣ ● ደንበኞች ግብይት/ክፍያዎች በሚፈፅሙበት ግዜ ወዲያውኑ ክፍያ/ግብይት እንደፈፀሙ የሚያሳውቁ መልእክቶች ወደ ስልካቸው እንደደረሳቸው ማረጋገጥ:: እነዚህ መልእክቶች በተለያየ ምክንያቶች እክል ገጥሟቸው ሳይደርሱ ሲቀሩ የባንክ አካውንት በመግባት ሒሳብዎን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል:: በሌላ አባባል የባንክ ሂሳቦችዎን እና ግብይቶችዎን ገብተው እስካልፈተሹ ድረስ የክፍያ ማረጋገጫው የሚገልፅ የጽሑፍ መልእክት ሁሉ ህጋዊ/እውነተኛ ነው ብለው አያስቡ፣ ● የሚጠቀሙባቸዉን ሲም ካርዶች በይለፍ ቃል መቆለፍ።