አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሣይተዋወቁ አንዳቸውን የሌላቸውን ሕይዎት ያተረፉ እንግሊዛዊና ጀርመናዊ ተገናኙ፡፡
ነገሩ እንዲ ነው፡፡ ዶክተር ኒክ ኢምበልተን ለዓመታት ለብዙዎች ፈውስ በመሆን የታመመን አካልና አዕምሮ ሲጠግን ኖሯል፡፡ በዚህም ስራው ለሺዎች ደርሷል፡፡
ሆኖም በአስደንጋጭ ሁኔታ ሀኪሙ ኒክ ኢምበልተን ሀኪም አስፈለገው፤ በደም ካንሰር በጠና ታመመ፡፡
ብቸኛ ተስፋውም የአጥንት-መቅኒ ንቅለ ተከላ ማድረግ እንደሆነ ተረዳ። ለዚህም የእንግሊዛውያን እገዛ እንደሚያስፈልገው ተለፈፈ፡፡ ሆኖም ለሀኪሙ የሚሆነው የአጥንት መቅኒ በመላው ሀገሪቱ በመብራት ቢታሰስ ታጣ፡፡
ያኔ ብዙ ርቀት እጓዛለሁ፣ ለሰዎች መዳን የበኩሌን ጠጠር አዋጣለሁ ብሎ ሲያምን የነበረ ሀኪም ተስፋው እየመነመነ ሲሄድ ታወቀው፡፡
በዚህም ቅስም ሰባሪ ዜናውን ለባለቤቱና ለልጆቹ የሚያረዳበት ጊዜ ደርሶ፤ ተናገረ፡፡ ሀዘን ሆነ፡፡
ሆኖም ከእንግሊዝ የታጣው የዶክተሩ ልክ የአጥንት መቅኒ ባህር ተሻግሮ ሊፈለግ ግድ ነው ተባለ፡፡ ተፈለገ፤ እንደእድል ሆኖ አንድ ደግ ከሰውነቱ ቆርጦ ሊያጋራው ፈቀደ፡፡
በዚህም ናታሊ ራይት የተባለው ጀርመናዊ በህይወት ዘመኑ አይቶት ለማያውቀው፣ ዘመድም ወዳጅም ላልሆነ ግለሰብ የሚያስፈልገውን አደረገ፡፡ በሱ የአጥንት መቅኔ ልገሳ ሀኪሙ በካንሰር ህመም ከመሞት ተረፈ፡፡
ይህም ታሪክ ለቢቢሲ ሁለት ደግ ልቦችን ለማገናኘት ምክንያት ሆነው፡፡ ተገናኙ፡፡
ዶክተር ኒክ ኢምበልተን በዚህ ጊዜ ሳግ በያዘው ድምጽ “አሁን ካንሰሩ እኔ ውስጥ የለም፤ ባትደርስልኝ ኖሮ ይሄኔ ልጆቼ ያለአባት ያድጉ ነበር ፤ አመሰግንሃለሁ” አለው፡፡
ማሪዮስ ምስጋናውን በመቀበል “አንተም የሰራኸውን አታውቅም፤ የኔን ህይዎት ሳታውቅ አትረፈሃል” አለው፡፡
እንዴት ለሚለው የብዙዎች ጥያቄም መልስ ሰጠ፡፡ ራሱን ሊያጠፋ እንደነበርና ምክንያቱም ከ13 ዓመቱ ጀምሮ የነበረበት የአዕምሮ ህመም እንደሆነ ገለጸ፡፡
“በምድር ላይ የመኖሬ ትርጉም ምንድነው ለሚለው ጥያቄ መልስ አልነበረኝም፤ አሁን ግን ይሄን በማድረጌ ደስተኛ ነኝ” ብሏል፡፡
በዚህም የማይተዋወቁት ግለሰቦች አሁን ላይ በተጋሩት ደም ወንድማማቾች ሆነው ሊቀጥሉ በልባቸው ተማምለዋል፡፡