አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከደቡባዊ ትብብር ድርጅት (ኦ ኤስ ሲ) ጋር አብራ ለመሥራት የሚያስችላትን ስምምነት ተፈራርማለች።
ስምምነቱን የፈረሙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እና የደቡባዊ ትብብር ድርጅት ዋና ፀሐፊ መንሱር ቢን ሙሳለም ናቸው፡፡
ስምምነቱም በደቡባዊ ትብብር ድርጅት አባል ሀገራት መካከል የአቅም ግንባታ፣ ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሳይንስና ቴክኖሎጂ የትምህርት ዕድሎችን በማመቻቸት እና የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ለማስቻል ብሎም የዘርፉ ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት እንደሚያግዝ ተገልጿል፡፡
ከስምምነቱ ጎን ለጎንም በደቡባዊ ትብብር ድርጅት የተሠራው የደቡብ ለደቡብ የትምህርት ማበልፀጊያ ማዕክል አካታች የትምህርት አሰጣጥን ለመደገፍ የሚረዳ የቴክኖሎጂ ውጤት ተመርቋል፡፡
በዚሁ ወቅት በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር÷ ኢትዮጵያ ጥራት ያለው የትምህርት ሥርዓት ለመገንባት ጥረት እያደረገች መሆኗን ማስረዳታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በደቡባዊ ትብብር ድርጅት የተጀመሩ ሥራዎች ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የዘረጋችውን ዕቅድ ለማሳካት የቴክኖ-ዲጂታል አማራጮች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም አስገንዝበዋል፡፡
መንሱር ቢን ሙሳለም በበኩላቸው÷ ድርጅቱ ያስመረቀው ቴክኖሎጂ ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለድርጅቱ አባል ሀገራት ባለሙያዎችና ተባባሪ አባላት በትምህርት ሥርዓቱ የአጋዥነት ሚና የሚጫዎቱ ሥራዎችን ለመሥራት ይረዳል ብለዋል።
የተመረቀው ቴክኖሎጂው የትምህርት አሰጣጥን ለመደገፍ የሚረዳ፣ በየሀገራቱ በትምህርት ዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመፍታት በሰባት ቋንቋዎች የሚሠራ እና ከክፍያ ነፃ ዲጂታል የትምህርት መሣሪያዎች ማዕከል መሆኑም ተብራርቷል፡፡