አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም የፀጥታ መዋቅር የፍትሀዊነትና የአካታችነትን ጥያቄ ሊመለስ ይገባል ሲሉ የአፍሪካ ሕብረትን ለቀጣይ አንድ ዓመት በሊቀመንበርነት የሚመሩር የሞሪታኒያው ፕሬዚዳንት መሀመድ ኦውልድ ጋዝዋኒ ገለጹ።
ባለፉት ሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ መዝጊያ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት መሀመድ ኦውልድ ጋዝዋኒ፤ ጉባኤው ከትምህርት ጉዳዮች በተጨማሪ በሰላም፤ ፀጥታ እና ዘላቂ ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ መምከሩን ተናግረዋል።
አፍሪካ በዓለም መድረክ ድምጿን ለማሰማት በተባበሩት መንግስታት ፀጥታ ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንደሚያስፈልጋት አስገንዝበዋል።
የዓለም የፀጥታ መዋቅር የፍትሀዊነትና የአካታችነትን ጥያቄ ሊመለስ ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካን ችግርች ለመፍታት የተያዙ ዕቅዶች መተግበር እንዳለባቸው ገልጸው፤ ሀገራት የልማት ተግባሮቻቸውን ከአጀንዳ 2063 ጋር የተናበቡ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።