የሀገር ውስጥ ዜና

60 በመቶ ያህሉን ክትባት በአፍሪካ ለማምረት ፕሮግራም መቀረጹ ተገለጸ

By Amele Demsew

February 18, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፈረንጆቹ 2040 ስልሳ በመቶ የሚሆነውን ክትባት በአፍሪካ ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ፕሮግራም መቀረጹን የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በ37ኛው የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ፍትሐዊነት፣ ራስን መቻልና የሕዝብ ጤና ጥበቃ ላይ ያተኮሩ ሦስት ወሳኝ ነጥቦች ለጉባዔው እንደሚቀርቡም የኮሚሽኑ ዳይሬክተር ዶክተር ጂን ካሲያን (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የመጀመሪያው በሀገር ውስጥ ማምረትን እንደሚመለከት ጠቁመው÷ ለዚህም ”አጋርነት ለአፍሪካ ክትባት” የተሰኘ መርሐ-ግብር መቀረጹን እና በ2040 ስልሳ በመቶ የሚሆነውን ክትባት በሀገር ውስጥ ለማምረት መታሰቡን ጠቅሰዋል፡፡

ቀጣዩ ነጥብ ፍትሐዊ ገበያን መፍጠር መሆኑን አመላክተው÷ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ያለ ሃብት እና ፖለቲካዊ አቋም ልዩነት ፍትሐዊ የመድሃኒትና ክትባት የሚያገኙበትን ሥርዓት መፍጠር ነው ብለዋል፡፡

ሦስተኛው ነጥብ አፍሪካን ከድንገተኛ ወረርሽኝ ለመከላከል ያላትን ዝግጁነት ለማሳደግ የድንገተኛ ወረርሽኝ ፈንድ አስፈላጊ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል፡፡

እነዚህ ነጥቦች የአፍሪካ የጋራ ፍላጎቶች መሆናቸውን በመገንዘብ ሕብረቱ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የኤች አይ ቪ ቫይረስ አሳሳቢነት ላይ ከ30 በላይ የሀገራት ጤና ሚኒስትሮች ጋር ውይይት በማድረግ ሀገራቱ ልምዶቻቸውን አካፍለዋል ነው ያሉት፡፡

በመራኦል ከድር