አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚገባትን ቦታ እንድታገኝ ሕብረቱ እና አባል ሀገራት ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ መሐመት ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ በ37ኛው የሕብረቱ ጉባዔ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግገር÷አፍሪካ አሁን ያለችበትን የሰላም እጦት በትኩረት አንስተዋል፡፡
አፍሪካ ጠንካራ፣ ሰላማዊት እና የበለፀገች እንድትሆን ሁሉም አካላት እጅ ለእጅ ተያይዘው መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡
በየጊዜው እየተበራከቱ የመጡት መፈንቅለ መንግሥታት እና በታጠቁ ኃይሎች የሚደረጉ ግጭቶች አህጉሪቱ ወደ ፊት እንዳትሄድ እንዳደረጋት ገልጸዋል፡፡
ህብረቱ በግጭትና በጦርነት ምክንያት በንፁሃን ላይ የሚፈፀሙ ግድያና ስደት በፅኑ እንደሚያወግዝም ተናግረዋል።
ዓለም አቀፋ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በአፍሪካ ላይ የሚያደርገውን ኢ-ፍትሃዊ ተግባር ሁሉም ሀገራት ሊያወግዙት ይገባል ሲሉም አክለዋል።
ሱዳንን ጨምሮ በተለያዩ የህብረቱ አባል ሀገራት ያለው ቀውስ እንዲያቆም ምሁራንን ጨምሮ የቀጣናው የፖለቲካ አደረጃጀቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ሊቀመንበሩ ጠይቀዋል።
የአፍሪካ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በተለያዩ ሀገራት እየታየ ያለው አለመረጋጋት እንዲቆም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
አፍሪካ በርካታ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው፤ አንድነትን በማጠናከር የጋራ ልማትና እድገት ማረጋገጥ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
አንድነቷና ነፃነቷ የተጠበቀች አፍሪካን እውን ለማድረግ ሁሉም የበኩሉን ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት።