ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሩሲያ የካንሰር መከላከያ ክትባት ለማግኘት መቃረቧን አስታወቀች

By Meseret Awoke

February 15, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው የካንሰር መከላከያ ክትባት ለማግኘት መቃረቧን ገልጸዋል፡፡

በሞስኮ በፊውቸር ቴክኖሎጂ ፎረም ላይ ስለ ሩሲያ የህክምና ሣይንስ ወቅታዊ ሁኔታ ያነሱት ፕሬዚዳንት ፑቲን፥ ካንሰርን አስቀድሞ በመለየት እና በማከም ረገድ ከፍተኛ እመርታ መታየቱን ጠቁመዋል፡፡

ይህም ከካንሰር የመዳን ደረጃን ከፍ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት፡፡

“በተጨማሪም ኦንኮ-ክትባት ተብሎ የሚጠሩትን የካንሰር መከላከያ ክትባቶችን እና የበሽታ መከላከያ መድሃኒቶችን ለማግኘት ተቃርበናል” ብለዋል።

በዚህም በቅርቡ ውጤታማ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

እንደፕሬዚዳንቱ፥ በሩሲያ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የካንሰር ሁኔታዎች በመጀመሪያዎቹ ደረጃዎች እንደሚገኙም ነው የተናገሩት፡፡

በቀጣይም የህክምና ምርምር እና ልማት በሚፈለገው ደረጃ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

‘’ከአሁን በፊት ስለእነዚህ ነገሮች ማንበብ የምንችለው በምናባዊ ልብ ወለድ ብቻ ነው’’ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ አሁን ላይ ግን ይህ ሁሉ እውነታ እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡

በቅርብ ጊዜ ውስጥ በህክምና ዘርፉ እውነተኛ አብዮት ያመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡

ከፈጠራዎቹ ውስጥ አንዱ በአንጎል ውስጥ ከተተከለ የሰውን የእይታ አቅም ወደነበረበት መመለስ የሚችል ልዩ ቺፕ ነው ያሉ ሲሆን፥ ቴክኖሎጂው በአሁኑ ጊዜ ክሊኒካዊ ሙከራዎችን እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በመድሃኒት፣ በሽታን በመከላከል እና በሕክምናው መስክ የተመዘገቡ እድገቶች ቀጣይነትና ተጠቃሚነት የሌሎችን ኢንዱስትሪ ዘርፎች ተሳትፎ ይጠይቃሉም ብለዋል።

በዚህም ሞስኮ እነዚህን ቁልፍ የኢንዱስትሪ መስኮች እንደ ብሔራዊ ጠቀሜታ ፕሮጀክቶች አድርጋ እንደምትመለከታቸው ነው የጠቆሙት፡፡

አጠቃላይ የኢንዱስትሪ ሂደቱን በየደረጃው ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን ሠራተኞች ማሰልጠን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ለዘርፉ እንደሚያበረክት መግለጻቸውን የዘገበው አርቲ ኒውስ ነው፡፡

#Russia #Cancer

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!