Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአማራ ክልል ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ዜጎች የዕለት ድጋፍ እንደሚፈልጉ ተገለጸ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ከ2 ሚሊየን 400 ሺህ በላይ የዕለት ድጋፍ የሚሹ አርሶ አደሮችና ተፈናቃዮች መኖራቸውን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ።

በ2015/16 የመኸር እርሻቸው የወደመባቸው የዕለት ድጋፍ የሚሹ የሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ድጋፍ ያልቀረበላቸው መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቅሬታ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ፍቅሬ ሙሉጌታ÷ በክልሉ በተፈጥሮ አደጋ ሰብላቸው የወደመባቸው ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ከ600 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች የዕለት ድጋፍ የሚሹ መሆኑን ኮሚሽኑ በልይታ አረጋግጧል ነው ያሉት፡፡

በተፈጥሮ አደጋ ሰብላቸው የወደመባቸው እና ተፈናቃዮች በክልሉ ዘጠኝ ዞኖች እና 43 ወረዳዎች እንደሚገኙም አንስተዋል፡፡

ለእነዚህ ዜጎች ባለፉት 6 ወራት ከፌዴራል መንግስት የተመደበ ከ307 ሺህ ኩንታል በላይ የዕለት ምግብ ለማቅረብ ቢሞከርም ድጋፍ ፈላጊዎችን ሙሉ በሙሉ ማዳረስ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ለመጠባበቂያ ከተያዘ የምግብ ክምችት ውስጥ ከ38 ሺህ ኩንታል በላይ እህል ለ281 ሺህ ድጋፍ ፈላጊዎች መድርሱንም ጠቅሰዋል፡፡

ለዚሁ ድጋፍ ክልሉ ከ430 ሚሊየን ብር በላይ መድቦ የዕለት ደራሽ ምግብ ገዝቶ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ድጋፍ አልደረሰንም ያሉ አርሶ አደሮችን ቅሬታ በተመለከተም ችግሩ መኖሩን አምነው፤ይህም በአካባቢው ባለው የሰላም እጦት ምክንያት በተከሰተ የትራንስፖርት ችግር የተፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን በመፍታት ለተጎጂዎች የዕለት ደራሽ ምግብ ለማሰራጨ ትኮሚሽኑ በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

በግርማ ነሲቡ

Exit mobile version