Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የምንችልበት አቅም ላይ ነን – አቶ ይርጋ ሲሳይ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የምንችልበት አቅም ላይ ነን ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ ገለጹ።

የክልሉ ወቅታዊ የፖለቲካና የፀጥታ ሥራ ያለበትን ደረጃ የሚገመግም መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡

ክልሉ የገጠመውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የአመራሩን ቁርጠኝነት በጥልቀት በመገምገም መምራት ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ መሆኑ በመድረኩ ተነስቷል።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ እንዳሉት÷ መድረኩ ክልሉ ከችግር ለመውጣት የሕዝቡን ፍላጎትና የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በጥልቀት መረዳትን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

አሁን የሚያስፈልገው ኃላፊነትን በአግባቡ በመረዳት በቁርጠኝነት መሥራት ነው ብለዋል።

ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የምንችልበት አቅም ላይ ነን ያሉት ሃላፊው፤ ክልሉን ለማተራመስ የሚሠሩ ሃይሎች ከሕዝብ ተነጥለዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የሕዝብ ፍላጎት ሰላምና ልማት መሆኑ በክልሉ በተካሄዱ ሕዝባዊ ውይይቶች የተረጋገጠ መሆኑም በመድረኩ የተነሳ ሲሆን ችግሩን ለመቀልበሥ ሃይል የማሰባሰብ ሥራ ተሠርቷልም ተብሏል።

በተደረገው የሰላም ጥሪ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታጣቂ ሰላምን ፈልጎ የተሃድሶ ስልጠና መውሰዱን ገልጸዋል፡

በተጨማሪም የተበተኑ የክልሉ የፀጥታ ሃይል አባላት በተላለፈው ጥሪ መሰረት ተመልሰው የክልሉን ሕዝባዊ ፖሊስ መቀላቀላቸውና ሕዝቡ የመንግሥትን አስፈላጊነት አምኖ በመንቀሳቀሱ በፀጥታው በኩል ውጤት መገኘቱ ተነስቷል።

አሁን የተገኙትን የፖለቲካና የፀጥታ ድሎች ጥልቀት እንዲኖራቸው ለማስቻልም የአመራር አቅምን በማሳደግ መንግሥታዊ መዋቅርን ማጠንከር፣ የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ፣ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ መሥራትና የሥራ ዕድል ፈጠራን ማስፋት እንደሚያስፈልግ በመድረኩ ተነስቷል፡፡

በደሳለኝ ቢራራ

Exit mobile version