አዲስ አበባ፣ የካቲት 04፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮትዲቯሩ አጥቂ ሰባስቲያን ሃለር ከካንሰር ሕመም በማገገም ሀገሩ የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን እንድትሆን የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል፡፡
የቀድሞው የአያክስ እና ዌስትሃም አጥቂ ሰባስቲያን ሃለር የጀርመኑን ክለብ ቦርሺያ ዶርትሙንድ ከተቀላቀለ በኋላ በፈረንጆቹ ሐምሌ ወር 2022 የቴስቲኩላር ካንሰር ሕመም አጋጥሞት ነበር፡፡
ለሕመሙ ከሚሰጠው ሳይንሳዊ ትንታኔ እና በእግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ ከሚፈጥረው የአካል ብቃት ተፅዕኖ አንፃር ብዙዎቹ የኮትዲቯሩን አጥቂ የእግር ኳስ ሕይወት በ28 ዓመቱ እንደሚያበቃ ገምተው ነበር፡፡
የሃለርን የእግር ኳስ ጉዞ በመርሳት ፈጣሪ በሕይወት ብቻ እንዲያኖረው የጸለዩ የእግር ኳስ አፍቃሪያንም አልጠፉም፡፡
ነገር ግን የታሰበው ሳይሆን ሃለር የቀዶ ጥገና እና የጨረር (ኬሞቴራፒ) ሕክምናውን በማጠናቀቅ በፈረንጆቹ 2023 ጥር ወር ሕመሙን ታግሎ በማሸነፍ ሙሉ በሙሉ ከካንሰር ነጻ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
ለተጫዋቹ የተሳካ የኬሞቴራፒ ሕክምናም የጀርመን ሐኪሞች ጥረት ከፍተኛ እንደነበር ነው የተነገረው፡፡
ከካንሰር ሕመሙ ካገገመ በኋላ ወደ ማርቤላ የልምምድ ሜዳ በመመለስ በቦርሺያ ዶርትሙንድ የቡድን አጋሮቹን በመቀላቀል በቡንደስሊጋው ድንቅ ጊዜን ማሳለፍ ችሏል፡፡
በ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የእናት ሀገሩን ጥሪ የተቀበለው የ28 ዓመቱ አጥቂ ሰባስቲያን ሃለር ወደ አቢጃን በመመለስ የብሔራዊ ቡድን አጋሮቹን ተቀላቅሏል፡፡
ሃለር ደካማ አጀማመር በማሳየት ከምድብ በምርጥ ሶስተኝነት ያለፈው የኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን በግማሽ ፍጻሜው ዴሞክራቲክ ኮንጎን 1 ለ 0 ሲያሸንፍ ብቸኛዋን ግብ በማስቆጠር ቡድኑን ለፍጻሜ አሳልፏል፡፡
በፍጻሜው ከናይጄሪያ ጋር በነበረው ጨዋታ ኮትዲቯር በቁርጥ ቀን ልጇ ሰባስቲያን ሃለር ሁለተኛ ግብ በመታገዝ ናይጄሪያን 2 ለ 1 በማሸነፍ ያዘጋጀችውን የ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማንሳት ችላለች፡፡
52 ጨዋታዎች ተካሂደው 119 ግቦች የተቆጠሩበት 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኮትዲቯር ሻምፒዮንነት ትላንት ምሽት ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡