Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የዓድዋ ድል መታሰቢያው እስካሁን ባለመገንባቱ ያስቆጫል- ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል ከሀገርና አኅጉር ተሻግሮ በዓለም የተስተጋባ አኩሪ ድላችን ቢሆንም ይህን በአንድ ቦታ በአግባቡ የሚገልጽ የዓድዋ ድል መታሰቢያ አለመገንባቱ የሚያስቆጭ ነው ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ፒያሳ የተገነባውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ መርቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሣኅወርቅ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የእኛ ብቻ ሳይሆን ለነጻነት፣ ለሕዝቦች እኩልነት ተስፋን የሰጠ ድል ነው ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህን ድል ይዘን እስካሁን ታሪካችንን የሚመጥን ሥራ ባለመከናወኑ ያስቆጫል ነው ያሉት፡፡

ዛሬ ላይ የዓድዋን ድል ታሪክ በሚመጥን አግባብ መታሰቢያ መገንባቱን ጠቅሰው÷ ለዚህም ሐሳብ ከማመንጨት ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደረጉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደርን አመስግነዋል፡፡

ታሪክን በቅጡ በመረዳት እንደ ዓድዋ አስተሳሳሪ እና አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ መትጋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ምናልባት የሐሳብ እና የፍላጎት ልዩነት ቢኖር እንኳ የመጀመሪያው ምርጫ ውይይት እንጂ ጠመንጃ ሊሆን እንደማይገባም ነው ያስረዱት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

Exit mobile version