አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ያለምንም አገልግሎት ለዘመናት በኖረው ስፍራ ዘመን የማይሽረው ሥራ ሠርተናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ፒያሳ የተገነባውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ መርቀዋል፡፡
ምረቃውን ተከትሎም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባደረጉት ንግግር÷ ያለምንም አገልግሎት ለዘመናት በኖረው ስፍራ ዘመን የማይሽረው ሥራ እንዲከናወንበት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስገንዝበዋል፡፡
የዓድዋ ድል መታሰቢያ ታሪኩን በሚመጥን ሁኔታ ደረጃውን ጠብቆ መገንባቱንም አንስተዋል ከንቲባዋ፡፡
የዓድዋ ጀግኖች ያለልዩነት በጋራ የጻፉት ድል ማስረጃዎች በአግባቡ ባለመሠነዳቸውና ባለመነገራቸው ምክንያት ዝንፈት መኖሩን አስታውሰዋል፡፡
በመሆኑም በዓድዋ ድል መታሰቢያ ትክክለኛ ማስረጃዎችን በማካተት እና የታሪክ ክፍተትንም በሚሞላ አግባብ ሥራዎች በትኩረትና ጥንቃቄ መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለጎብኚዎች ተጨማሪ መዳረሻ መሆኑን ጠቁመው÷ ለውጤታማነቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው