ስፓርት

የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ይጠናቀቃል

By ዮሐንስ ደርበው

February 11, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮትዲቯር አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል፡፡

በማጠቃለያ መርሐ-ግብሩም ናይጄሪያ ከኮትዲቯር ለፍጻሜ የሚያደርጉት ጨዋታ አጓጊ ሆኗል፡፡

ጨዋታው ምሽት 5፡00 ሠዓት ላይ 60 ሺህ ተመላክቾችን የማስተናገድ አቅም ባለው ኦሊሳን ኦታራ ስታዲየም ይደረጋል።

ከፍጻሜው ጨዋታ በፊት የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት እንደሚካሄድ የወጣው መርሐ-ግብር ያስረዳል፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የፍጻሜ ውድድሩን ለሚያሸንፍ ሀገር የ7 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም ሁለተኛ ለሚወጣ ሀገር 4 ሚሊየን ዶላር ሽልማት ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

በግማሽ ፍጻሜው የወደቁ ሁለት ሀገራት እያንዳንዳቸው 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር፤ በሩብ ፍጻሜው የተሰናበቱ አራት ሀገራትም እያንዳንዳቸው 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር እንደሚሸለሙም ተመላክቷል፡፡

ትናንት በተካሄደ የደረጃ ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ ዴሞክራቲክ ኮንጎን በመለያ ምት 6 ለ 5 በማሸነፍ 3ኛ ደረጃን በመያዝ ነሐስ አግኝታለች፡፡