Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የዓድዋ ድል መታሰቢያ የጀግንነት ታሪክ አስጠብቆ የሚያቆይ ትውልድ ተሻጋሪ ሥራ ነው – አባት አርበኞች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል መታሰቢያ ታሪክ ሰሪዎችን ያከበረና ትውልድ ተሻጋሪ የሆነ ትልቅ ሥራ መሆኑን ሙዚየሙን አስመልክቶ አስተያየት የሰጡ አባት አርበኞች ገለጹ።

ታሪኩን በሚመጥን መልኩ የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ግንባታው ተጠናቆ ነገ ይመረቃል።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ የዓድዋ ሰንሰለታማ ተራሮችን፣ የዓድዋ ፈረሰኞች ማስታወሻ፣ ለሴት ጀግኖች ክብር የተሰየመ ማስታወሻ፣ የአንድነት ማዕከል፣ የአፍሪካ ነፃነት ማስታወሻ እንዲሁም የጀግኖችን ጉዞ የሚያሳዩ ድንቅ የታሪክ አሻራዎችን በውስጡ ይዟል።

መታሰቢያ ሙዚየሙ የጀግንነት ታሪክ አስጠብቆ የሚያቆይ ትውልድ ተሻጋሪ ሥራ መሆኑን ነው አባት አርበኞች የገለጹት።

አባት አርበኛ መኮንን መሸሻ እንዳሉት÷ለአፍሪካውያን የነጻነት ተምሳሌት ለሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ መገንባቱ ታሪክ የሰሩትን በማክበር ትውልዱ በቀጣይ ሌላ አገርን የሚጠቅም ታሪክ እንዲሰራ የሚያግዝ ነው።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ መገንባቱ በተለይም ለወጣቱ ትልቅ ቅርስና የቱሪዝም መዳረሻ እንደሚሆንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ወጣቱ የልማት አርበኛ በመሆን ሳይሰለች አገሩን ማገልገልና የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ማስጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።

አባት አርበኛ ሃምሳ አለቃ ዲባባ ጫላ በበኩላቸው÷ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሁሉንም ታሪኮች አሟልቶ የያዘና ትውልዱ የሚማርበት ትልቅ ሥራ መሆኑን አመልክተዋል።

ዓድዋ የደም ዋጋ የተከፈለበትና የጥቁር ሕዝቦች ነጻነት እንዲሁም የድል ምልክት ነው ያሉት አባት አርበኛው መታሰቢያው የተሰራውን የጀግንነት ታሪክ አስጠብቆ የሚያቆይ ነው ብለዋል።

አባት አርበኞቹ ወጣቱ ትውልድ የዓድዋ ድል መታሰቢያን በአግባቡ በመጠበቅ ለትውልድ ማሻገር እንዳለበት ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version