የሀገር ውስጥ ዜና

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት የስራ ሰዓት ማሻሻያ አደረገ

By Tamrat Bishaw

February 09, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት የስራ ሰዓት ማሻሻያ ይፋ አደረገ።

አገልግሎቱ ዘወትር ከሰኞ እስከ አርብ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ድረስ ለደንበኞች አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታውቋል።

በተጨማሪም ቅዳሜ ግማሽ ቀን ብቻ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት ወደ ሙሉ ቀን በማሻሻል እስከ 11 ሰዓት ተኩል ድረስ በሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ 14 እንዲሁም በድሬዳዋ አንድ በድምሩ 15 ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች እንዳሉ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሀሚድ ኪኒሶ፤ ተቋሙ የተሰጠውን ሀላፊነት ለመወጣት አሰራሩንና አደረጃጀቱን በማሻሻል የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ዛሬ በይፋ የተጀመረው የሰዓት ማሻሻያም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ የተሻሻለው አገልግሎት ዘወትር ከጠዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ ምሳ ሰዓትን ጨምሮ እስከ ምሽት 1 ሰዓት በአዲስ አበባ ዋና መስሪያ ቤት እና በድሬዳዋ ቅርንጫፍ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቅዳሜ ሙሉ ቀን እስከ 11:30 ደግሞ በሁሉም ቅርንጫፎች አገልግሎት ይሰጣል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የሰዓት ማሻሻያው በሌሎች ቅርንጫፎች በሂደት እንደሚጀመር አመላክተዋል።

የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታው በላይሁን ይርጋ በበኩላቸው ተቋሙ በተለይ ሀሰተኛ ሰነዶችን በማጥራት ረገድ ጉልህ ሚና እየጫወተ እንደሚገኝ ገልጸው፤ አሁን ያደረገው የስራ ሰዓት ማሻሻያ እየጨመረ የመጣውን ተገልጋይ በተገቢው ለማስተናገድ እንደሚያስችለው ተናግረዋል።

ሳሙኤል ወርቃየሁ

#Ethiopia ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!