አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወራት 7 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለፀ ፡፡
የተቋሙ የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ተገምግሟል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በመድረኩ እንዳሉት÷ የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት የሚያውኩ እና ዜጎች ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርጉ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በመቆጣጠር ረገድ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በተደረጉ መጠነ ሰፊ የኦፕሬሽን ስራዎች በርካታ ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ትላልቅ ፋብሪካዎች፣ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ሌሎች በርካታ የፌደራል ተቋማትን ለመጠበቅ የተደረገው ጥረት የተሳካ እንደነበርም አንስተዋል።
በተጨማሪም መንገዶች፣ ሆስፒታሎች እና በከፍተኛ በጀት የሚገነቡ ግዙፍ ልማት ፕሮጀክቶች በፀረ-ሰላም ኃይሎች ሳይደናቀፉ በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቁ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመከላከል በተደረገው እንቅስቃሴም ውጤት መገኘቱ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው የሥራ መመሪያ መስጠታቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡