አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሀገራት ለሰላም መስፈን በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ዋና ፀሐፊው በኒውዮርክ በሚገኘው የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት በፈረንጆቹ 2024 ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮችን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም በተመድ ቻርተር እና በዓለም አቀፍ ህግጋት መሰረት ሰላም እንዲሰፍን መስራት አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ፤ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እንሰራለን ብለዋል።
በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው መምከራቸውን ጉተሬዝ ተናግረዋል፡፡
ዝርዝር አጀንዳው ረጅም ቢሆንም ሰላም ሁሉን በአንድነት የሚያስተሳስር ወሳኝ ነገር በመሆኑ በሁሉም አቅጣጫዎች ሰላም አስፈላጊ ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡
ይሁንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ግጭት፣ ሰላምና ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ጂኦፖለቲካዊ ክፍፍሎች፣ ማህበረሰብን የከፈለው ዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ የሰላም ሁኔታን የሚፈታተኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በተጨማሪም እየሰፋ የመጣው በፍትህና በሰላም ሽፋን የሚከሰት የፍትህ መጓደል እንዲሁም የዓለም በካይ ጋዝ ልቀት እና የሙቀት መጠን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረስ ሰላምን የሚፈታተኑ ክስተቶች ሆነዋል ብለዋል፡፡
በተቋማት፣ በመሪዎች እንዲሁም በመንግስታት እና በባለብዙ ወገን ተቋማት ላይ እምነት ሊኖር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የሰዎችን ችግር በመፍታት በሰዎች ህይወት እውነተኛ እና አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት የሚል የመፍትሄ ሀሳብ ማቅረባቸውንም ሲጂቲኤን ዘግቧል።