Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም የምረቃ ስነ-ስርዓትን ተከትሎ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ተደረጉ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 01፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የካቲት 03 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄደውን የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም የምረቃ ስነ-ስርዓትን ተከትሎ በዕለቱ ከቀኑ 6 ሰዓት ጀምሮ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ተደርገዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከየካቲት 03 እስከ 10 ቀን 2016 ዓ.ም የሚስተናገዱ ልዩ ልዩ ኩነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል በፀጥታ ዕቅድ ላይ ተወያይቶ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቋል።

በዚህም የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ልዩ ልዩ እንግዶች እና የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም በደማቅ ስነ-ስርአት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይመረቃል።

የምረቃ በዓሉን ተከትሎም በዕለቱ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳያጋጥም የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ እንደሚሆኑም የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት:-

ከአፍንጮ በር ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን፣

ከሰሜን ሆቴል ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን፣ከዮሃንስ ቤተ ክርስቲያን ወደ አቡነ ጴጥሮስ፣

ከአራት መንታ ወደ ጅንአድ፣

ከይርጋ ሃይሌ የገበያ ማዕከል ወደ አቡነ ጴጥሮስ፣

ከሃብተ ጊዮርጊስ ድልድይ ወደ ሱማሌ ተራ ፣

ከሱማሌ ተራ ወደ ኤሊያና ሆቴል(ባንኮዲሮማ) መስቀለኛ፣

ከተክለ ሃይማኖት አደባባይ ወደ ቴዎድሮስ አደባባይ መንገዶች የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 6 ሰዓት ጀምሮ ለተሽከርካሪ ዝግ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

እንዲሁም ከሀገር አስተዳደር መብራት (ኢሚግሬሽን) ወደ ቴዎድሮስ አደባባይ፣
ከንግድ ማተሚያ ቤት ወደ ቴዎድሮስ አደባባይ፣

ከአሮጌው ቄራ ወደ ባንኮ ዲሮማ መብራት፣

ከራስ መኮንን ድልድይ ወደ ደጎል አደባባይ፣

ከራስ መኮንን ድልድይ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን ፣

ከመቅደላ ሆቴል ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን፣

ከቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን ወደ ቴሌ እና ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን ፊት ለፊት ወደሚገኘው አደባባይ የሚወስዱት መንገዶች በተጠቀሰው ቀን እና ሰዓት ለተሽከርካሪ ዝግ ይሆናሉ ነው የተባለው፡፡

ስለሚሆኑ አሽከርካሪዎች ይህንን ተገንዝበው አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ እና የትራፊክ ፖሊሶች በሚጠቁሟቸውን አማራጭ አቅጣጫዎችን በመጠቀም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በዋዜማው የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም ከላይ በተጠቀሱት መንገዶችና የምረቃ ስነ-ስርዓቱ በሚከናወንበት በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ዙሪያ ተሽከርካሪ ማሳደርም ሆነ ለአጭርም ሆነ ለረጀም ሰዓት አቁሞ መሄድ የተከለከለ መሆኑንም አሳስቧል፡፡

ይለፍ ያላቸው አሽከርካሪዎች ቸርችር ጎዳና ጫፍ የቀድሞ ሜክሲኮ ታክሲ ተራ እና ከቴዎድሮስ አደባባይ እስከ ቸርችር ጎዳና ጫፍ መኪናዎቻቸውን መቆም የሚችሉ ሲሆን፤ ለጋራ ደህንነት ሲባል ፍተሻ እንደሚኖር በመገንዘብ ታዳሚዎች የተለመደ ትብብር እንዲያደርጉ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

በተጨማሪም የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ጥሪ ከተደረገላቸው እንግዶች ውጪ ወደ ሙዚየም የሚወስዱ መንገዶች ዝግጅቱ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ለእግረኞች ዝግ መሆናቸውን ፖሊስ አመላክቷል።

Exit mobile version