የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያና ፓኪስታን ወታደራዊ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ መሥራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ

By Melaku Gedif

February 09, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 01፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሻሪፍ የተመራ ልዑክ ከኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮማንዳንት ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱ በሁለቱ ሀገራት የተቋማት ግንኙነትና የጋራ ጥቅም ትብብር ላይ ያተኮረ መሆኑን ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የሀገራቱ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተሻለ እና ውጤታማ መሆኑን በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሻሪፍ ገልጸዋል።

የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ ዩኒቨርሲቲዎች የበለጠ በቴክኖሎጂ ሽግግር በስልጠና፣ በትምህርት፣ በጥናት እና ምርምር ለማዛመድ ያለመ ውይይት መሆኑንም ተናግረዋል ።

ተቋማቱ በመማር ማስተማሩ ላይ የበለጠ ራሳቸውን ማሳደግና ማዘመን በሚችሉ የስልጠና ፕሮግራሞች ውጤታማ ልምዶችን በመለዋወጥ ጭምር የጋራ ጥቅሞቻቸውን አብረው በጋራ ማረጋገጥ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡

አምባሳደር አቲፍ ሻሪፍ÷ በቀጣይ የሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ዩኒቨርሲቲዎች በአይሲቲ፣ በሳይበር ሴኪዩሪቲ፣ በአይሮቲካል ኢንጅነሪግና በመሳሰሉት የስልጠና ፕሮግራሞች ላይ በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮማንዳንት ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ በበኩላቸው÷ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የሠራዊቱን የልህቀት አድማስ ማረጋገጥ በሚችሉ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ከተጓዳኝ ተቋማት ጋር በቴክኖሎጀ ትስስር በማዛመድ ተጨባጭ ጥናትና ውጤታማ ምርምር ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚመጡ ወታደሮችን ጭምር ተቀብሎ በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች ላይ እያስተማረ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

ተቋማቱ የጋራ ወታደራዊ ሙያን ማሳደግ በሚችሉ መጠነ ሰፊ ጉዳዮች ላይ አብረው በጋራ ስልጠናዎችን ማድረግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።