የሀገር ውስጥ ዜና

3ኛ አየር ምድብ ፀረ ሰላም ኃይሎችንና አልሸባብን በመደምሰስ ደማቅ ታሪክ ያለው ነው – ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

By Amele Demsew

February 08, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 3ኛ አየር ምድብ ፀረ ሰላም ኃይሎችንና አልሸባብን በመደምሰስ ደማቅ ታሪክ ያለው ነው ሲሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡

ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የ3ኛ አየር ምድብን የግዳጅ አፈፃፀምና የበረራ ተማሪዎችን የስልጠናን ሂደት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ሌተናል ጄኔራል ይልማ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ÷ ምድቡ ሀገራችንን ለማተራመስ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ቡድኖችን ሴራ ከማክሸፉም በተጨማሪ ፅንፈኛውን የሶማሊያ አሸባሪ አልሸባብን በመደምሰስ ሰላማችን እንዲረጋገጥ ወሳኝ ድርሻውን ተወጥቷል።

የበረራ ተማሪዎቹ ስልጠናቸውን በአግባቡ በመወጣት የተቋሙን ተልዕኮ ከግብ ማድረስ እንደሚያስፈልግም ነው ያነሱት፡፡

ቀጣይ በስትራቴጂክ ደረጃ እንደ ሀገር ለሚሰጠን ግዳጅም ታሳቢ ያደረገ የወትሮ ዝግጁነት አቅም ልክ ሁሉም የምድቡ አመራር እና አባላት መዘጋጀት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

3ኛ አየር ምድብ የደማቅ ተጋድሎ ታሪክ ባለቤት የሆኑ አብራሪዎችና የአቪዬሽን ሙያተኞች መፍለቂያ መሆኑንም ሌተናል ጄኔራል ይልማ በጉብኝታቸው ወቅት መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በኢፌዴሪ አየር ኃይል የ3ኛ አየር ምድብ አዛዥ ሌተናል ኮሎነል ደረጀ ቡሽሬ በበኩላቸው ÷ በአየር ምድቡ ከለውጡ ወዲህ የተገኘውን ምቹ የስራ ድባብ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ትላልቅ ስራዎች መከናወናቸውንና የተሻለ የግዳጅ አፈፃፀም መወጣት በሚያስችል ቁመና ላይ መገኘቱን ገልፀዋል፡፡