የሀገር ውስጥ ዜና

10ኛው ሀገር አቀፍ የህብረት ስራ ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም መካሄድ ጀመረ

By Amele Demsew

February 08, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 10ኛው ሀገር አቀፍና 3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረት ስራ ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም መካሄድ ጀመረ።

ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲንፖዚየሙ “የህብረት ስራ ማህበራት ሚና ከገበያ በላይ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ እስከ የካቲት 5 ይቆያል ተብሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማስጀመሪያ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት÷ የህብረት ስራ ማህበራት ምርትን በጥራት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሁም በጊዜ ከማቅረብ አንፃር ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው ።

የህብረት ስራ ማህበራት የተቋቋሙለትን አላማ ከማሳካት አንፃር ክፍተት እንዳለባቸው ጠቁመው÷ ችግሩን ለመፍታት የሪፎርም ስራ በመስራት የወቅቱን ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የህብረት ስራ ማህበራት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንዲህ አይነት መድረኮች ደግሞ የገበያ ትስስርን ለማሳደግ እድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የህብረት ስራ ማህበራት ኮሚሽንና በአዲስ አበባ የህብረት ስራ ማህበራት በጋራ የተዘጋጀው ኤግዚቢሽንና ባዛር በስድስት ቀናት ቆይታው ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

በበረከት ተካልኝ