ስፓርት

የጃፓኗ ካሳማ ከተማ ከንቲባ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

By Meseret Awoke

February 08, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጃፓኗ ካሳማ ከተማ ከንቲባ ሺንጁ ያማጉቺ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተለያዩ የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

በጃፓን ካሳማ ከተማ ላለፋት ተከታታይ አምስት ዓመታት በታሕሳስ ወር በጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ በቂላ ለመዘከር የግማሽ ማራቶን ውድድር ይዘጋጃል ተብሏል፡፡

ከንቲባ ሺንጁ ያማጉቺ ዛሬ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተለያዩ የስፖርት ትጥቅ ድጋፎችን ያስረከቡ ሲሆን ፥ ለአትሌቶች ለስልጠና የሚሆናቸውን ትጥቆች በማምጣታቸው ደስ መሰኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

ትጥቆቹ የተሰበሰቡት በ2023 በካሳማ በተካሄደው የአበበ በቂላ መታሰቢያ ውድድር ላይ ከተሳተፉ መሆኑን ገልፀው ፥ በቀጣይ በየዓመቱ ድጋፉ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወ/ጊዮርጊስ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረ/ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ለተደረገውን ድጋፍ ማመስገናቸውን የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

በመርሐ- ግብሩ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ(ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረ/ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ የካሳማ ከተማ ከንቲባ ሺንጁ ያማጉቺ ተገኝተዋል።