ስፓርት

አሰልጣኝ ፍሬው ሀይለገብርኤል ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ተለያዩ

By Mikias Ayele

February 07, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን እና ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በይፋ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው በ2013 ዓ.ም የተሾሙት አሰልጣኙ፤ በአራት ዓመት ቆይታቸው ቡድኑ በፈረንጆቹ 2022 እና 2024 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያዎች እስከ መጨረሻው ዙር እንዲደርስ አስችለዋል፡፡

በተጨማሪም በ2022 በዩጋንዳ በተካሄደው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ውድድር አሸናፊ እንዲሆን አድርገዋል።

ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ በተጨማሪ ከግንቦት 2014 ጀምሮ የዋናው ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) አሰልጣኝ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን በቆይታቸውም የሴካፋ ሴቶች ዋንጫን በ3ኛ ደረጃ እንዲያጠናቅቅ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ፍሬው በቆይታቸው ላበረከቱት ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ምስጋና ያቀረበው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤ በቀጣይ መልካም እድል እንዲገጥማቸው ተመኝቷል፡፡